በዚህ ሳምንት የገጠመኝን ልንገራችሁ በአቢይ ጾም ይህን ያህል ሳቅ ምንድን ነው ማለታችሁ አይቀርም ነገር ግን እኔ ያየሁትን ነገር ጊዜ ገጥሟችሁ እናንተም ብታዩት ከዚህ የበለጠ ትገረሙ እና ትስቁ ነበር። ነገሩ ምንድን ነው ካላችሁ ነገሩ እንዲህ ነው እና አንቡት።
አንድ ቀን ከስራ እንደተመለስኩ ከደሳሳዋ ዶርሜ ቁጭ ብየ ሳለሁ በአጋጣሚ ቴሌቭዥን መክፈት ከዚያም ሪሞቱን እየነካካሁ ከላይ ወደ ታች ያሉ የቴሌቪዥን ቻናሎችን በመፈለግ ላይ ሳለሁ በአጋጣሚ አይኔ ላይ የሆነ ነገር ድቅን አለ። እኔም ምንድን ነው ብየ ስለተገረምኩ የሚተላለፈውን ነገር ማየት ጀመርኩ። ከዚያም "ስንት ሰው በዚህ እዚህ ግባ በማይባል ተረት ውስጥ ተደብቆ ይሆን?" ብየ እራሴን ጠየቅኩ። ሰዎች ያሉ የሆነ አዳራሽ ውስጥ ነው አንድ ሱፍ የለበሰ ሰውየ ከመድረክ ላይ ማይክ ይዞ እንደ አገሬ ፎካሪ ከወዲያ ወዲህ ይንጎራደዳል። እኔም ምን ሊያደርግ ነው? ብየ ስመለከት ከፍ ባለ ድምጽ እንዲህ ብሎ ጮኸ።
"አንች ከኋላ የቆምሽ ሴት" አለ። የሚገርመው ነገር ከኋላ የቆሙት ሴቶች ብዙ ነበሩ የትኛዋን ሴት እንደሆነ ግን ግልጽ አይደለም። ሰውየው የተናገረውን ነገር ስሰማ እና ስለ ጠንቋይ ሰዎች ሲያወሩ የሰማሁት ነገር ስለተመሳሰለበኝ እንዲህ ብየ አሰብኩ "በቃ ጠንቋይ እንዲህ በይፋ በመድረክ ላይ ማይክ ይዞ የማይሆን ተስፋ በመስጠት የዉሃንን ወደ ጨለማ ያመላልሳል።" ይህን እያሰብኩ እያለ ሰውየው ቀጠለ በድጋሜ "አንችን እኮ ነው" አለ የቆሙት ሴቶች ለራሳቸው ሳይገርማቸው አልቀረም። ምክንያቱም እርስ በራሳቸው ተያዩ እና ከመካከላቸው አንዷ "እኔን ነው?" አለች እሱም "አዎ አንችን ነው" አላት ከዚያም በመቀጠል "ከሰዓት ነው የመጣሽ አይደል?" አላት እሷም አዎ አለች። ከዚያም "የአባትሽ ስም ጌታቸው ነው የሚባል አይደል?" አላት እሷም "አዎ" አለች ከዚያም "የሆነ ነገር ቸግሮሻል አይደል? ስለምንድን ነው እንድጸልይልሽ የምትፈልጊ?" አላት እሷም ጥያቄው እውነት ስለመሰላት እንዲህ ብላ መለሰች "ልጆቸ በእዳ ስለተያዙ እዳቸው እንዲከፈል ነው" አለች የሚገርመው ነገር እሱ እና እሷ ቃለ ምልልስ በሚያደርጉበት ጊዜ ከመሀል "አሜን" የሚል ድምጽ ይሰማ ነበር። ይህንን ስሰማ ሰውየው ሰባኪ ሳይሆን ጠንቋይ መሆኑን በደንብ አረጋገጥኩ ምክንያቱም ከዚህ በፊት ጠንቋይ ቤት የሄዱ ሰዎች ጠንቋዩ በሚናገርበት ወቅት ታዳሚዎች "አሜን በእርስዎ መጀን" እያሉ የድለላ እና የሽወዳ ስራውን እንደሚያጅቡለት ሰምቻለሁ። ከዚያ በመቀጠለም ሰውየው እንዲህ በማለት ይፎክር ጀመር "በእየሱስ ስም የልጆችሽ እዳ ይከፈላል" ታዳሚዎችም አሜን በማለት ስብሰባውን አደመቁት። ይቆየን ይቀጥላል

No comments:
Post a Comment