Saturday, May 6, 2017

“እርሱ በተዋሕዶ ሰው የሆነ አምላክ ነው”

“እርሱ በተዋሕዶ ሰው የሆነ አምላክ ነው”፡፡ በሚል ርእስ በክፍል አንድ እና ሁለት ተዋሕዶን ሊቁ የተዋሕዶ አርበኛ ቅዱስ ጎርጎርዮስ እንዴት እንደገለጸው አይተናል፡፡ በዚህ ክፍል ደግሞ ሊቁ ቅዱስ ቄርሎስ ተዋሕዶን ለማስረዳት የመሰለውን ምሳሌ እናያለን፡፡ ከዚያ በፊት ግን ይህንን ጽሁፍ የምታነቡ ሰዎች እንድትረዱኝ የምፈልገው ነገር እኔ አባቶች በመጽሐፋቸው ላይ ያሰፈሩትን ነገር ሳልጨምር ሳልቀንስ እንደምጽፈው ልገልጽላችሁ እፈልጋለሁ፡፡ የቅባት ተከታዮች ግን እነሱ የማያውቁት ነገር ከሆነ ወይም እነሱ የሚሉትን የኑፋቄ ትምህርት የሚደግፍ መስሎ ካልታያቸው ምዕራፍ እና ቁጥር ጠቅሼ የጻፍኩትን ጽሁፍ የእራስህ ፍልስፍና ነው በማለት እነሱ እንደማይቀበሉት በክፍል አንድ እና ሁለት በሰጡት አስተያየት ላይ ለማየት ሞክሬያለሁ፡፡ ይህ ግን ፈጽሞ ከእውነት የራቀ ነው፡፡ ስለዚህ የእነሱን ማንነት ለመረዳት የሚጠቀሰውን ጥቅስ መጽሐፉ ላይ በመሔድ ማንበብ እና እውነት ወይም ሐሰት መሆኑን መረዳት ትችላላችሁ፡፡ወደ ምሳሌው ከመሔዴ በፊት የቅባት እምነት ተከታዮች ምስጢረ ስላሴ ላይ ያልገባቸው ነገር እንዳለ ትንሳኤ የሚባል ተከታያቸው ከጻፈው ጽሁፍ መረዳት ችያለሁ፡፡ ሌሎች የጻፋቸውን ነገሮች በሚቀጥሉት ከፍሎች እናያለን፡፡ መልካም ንባብ ካነበባችሁ በኋላ ሼር ማደረግን እንዳትረሱ ምክንያቱም ለሌሎች የድህነት ምክንያት ይሆናል እና ነው፡፡
ስላሴ ሶስት ከሚሆኑባቸው ነገሮች አንዱ የከዊን ሶስትነት ነው፡፡ ይህም ከዊነ ልብ፣ ከዊነ ቃል እና ከዊነ እስትንፋስ ናቸው፡፡ ምንም እንኳ ስላሴ በከዊን ሶሰት ቢሆኑም በህልውና በመገናዘብ ደግሞ እንድ ይሆናሉ፡፡ ይህም እንዴት ነው ብትሉ እንደሚከተለው ነው፡፡ ይህም ማለት በአብ ልብነት ወልድም መንፍስ ቅዱስም ያስቡበታል፡፡ በወልድ ቃልነት አብም መንፈስ ቅዱስም ይናገሩበታል፡፡ በመንፈስ ቅዱስ እስትንፋስነት(ሕይወትነት) አብም ወልድም ለዘለዓለም ሕያዋን ሆነው ይኖሩበታል፡፡ ይህ በስላሴ በህልውና የመገናዘብ ሁኔታ ቀድሞም አልተለያየም፡፡ አሁንም አልተለያየም፡፡ ወደፊትም ቢሆን አይለያይም፡፡ ይህና ያመጣሁበት ዋናው ምክንያት ሰው ምስጢረ ተዋሕዶን ለመረዳት መጀመሪያ ይህንን ረቂቅ ምስጢር መረዳት ስለሚገባ ነው፡፡ ትንሽ ስለረዘመ ነው ምሳሌው በክፍል አራት ይቀጥላል፡፡

ማስረጃ ወይስ ሰውን መሸወጃ


ክፍል ሁለት
1. መዝ 2÷7 “ እግዚአብሔር ይቤለኒ ወልድየ አንተ ወአነ ዮም ወለድኩከ” የሚለውን አዲሱ ሲተረጉም ፡- “እግዚአብሔር ይቤለኒ ወልድየ አንተ” ማለቱ እምቅድመ ዓለም ከአብ የተወለደውን ልደት ሲናገር ነው፡፡ “ወአነ ዮም ወለድኩከ” ማለቱ መለኮት ሰው ሲሆን በማኅጸነ እግዝእትነ ማርያም በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ የተወለደውን ልደት ሲናገር ነው፡፡ በማለት እንደ እራሱ ፈቃድ ይተረጉመዋል፡፡ ከዚህ በመቀጠል ደግሞ ከዳዊት አንድምታ ትርጓሜ መጽሐፍ ላይ ያለውን ትርጉም እንይ
መዝ 2÷7 “ እግዚአብሔር ይቤለኒ ወልድየ አንተ” ትርጉም አሁን አንተን አይሻም (ቃል ይቤ በል) ቅድመ ዓለም አካል ዘእም አካል ፣ ባህርይ ዘእም ባህርይ የወለድኩህ ልጄ ነህ አለኝ፡፡
“ወአነ ዮም ወለድኩከ” የሚለው ደግሞ ሲተረጎም ፡- አሁንም አነ ን አይሻም ዛሬም በተዋኅዶ የወለድኩህ ልጄ ነህ አለኝ፡፡ “ተውህቦ ለእግዚአብሔር ቃል ስም በስጋ ዘበ ህላዌሁ ይሰመይ” እንዲል ስለ ስጋ እንግድነት ሲገልጽ
አንድም፡-“ ሥጋ ይቤ” ይልና ፡- አንተ ሥጋ ቅድመ ዓለም አካል ዘእም አካል ባሕርይ ዘእም ባሕርይ የወለድኩህ ልጄ ነህ አለኝ፡፡ አንተ ልጄ ነህ ዛሬም በተዋህዶ ወለድኩህ ማለት በቃል ርስት፡፡
አንድም ፡- አሁንም አንተን እና አነን አይሻም(ስግው ቃል ይቤ)፡- ቅድመ ዓለም አካል ዘእም አካል ባሕርይ ዘእም ባሕርይ የወለድኩህ ልጄ ነህ አለኝ ፡፡ ዛሬም አውጻእኩከ አንሳእኩከ ሲል ነው፡፡ በትንሳኤ የወለድኩህ ልጄ ነህ አለኝ፡፡ አሁን ሁለተኛ የሚወልደው ሆኖ አይደለም በምሳሌ ተናገረው እንጅ ሰው ዘምቶ ያረጃል፤ በልቶ ያፈጃል፤ ህዝብን ሰብስቦ ልጁን አስጠርቶ ልጄ ‹‹ዘምቶ ያረጀ በልቶ ያፈጀ ›› ይሉሃል እኔ ነኝ፡፡ ‹‹በርስቴ ውጣበት ውረድበት›› ብሎ ይሰጠዋል፡፡ እሱም ወጣሁ ልጅ ነኝ ፈላሁ ጠጅ ነኝ ብሎ እግሩን ለጠጠር ደረቱን ለጦር ሰጥቶ ይዘምታል፡፡ በርስቱ ርስት በጉልቱ ጉልት ጨምሮበት ይመጣል፡፡ አባቴ በሰጠኸኝ ርስት ጉልት ጨምሬበት መጣሁ ይለዋል፡፡ እርሱም ቀድሞም ልጄ ዛሬም ልጄ ይልቅስ የዛሬው ይብለጥ ይለዋል፡፡ ጌታም ከአቤል ጀምሮ እስከ ዕለተ ዓርብ ያሉትን ነፍሳት “እለ ውስተ ሲኦል ፃዑ ወእለ ውስተ ጽልመት ተከስቱ ወርእዩ ብርሐነ ዐቢየ” በገነት አድርጎ ባረገ ጊዜ ልጄ ነህ አለው እንጅ፡፡
ወገኖቸ እንግዲህ እናንተ ፍረዱት ከመዝሙረ ዳዊቱ አንድምታ ላይ ያለው እውነታ ይህ ነው፡፡ መጽሐፉን ገዝታችሁ ማንበብ ትችላላችሁ፡፡ ከአንድምታው ላይ እንዳየነው “ወአነ ዮም ወለድኩከ” የሚለው “መለኮት ሰው ሲሆን በማኅጸነ እግዝእትነ ማርያም በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ የተወለደውን ልደት ሲናገር ነው” የሚል ትርጉም የለውም፡፡ ስለዚህ አዲሱ እና መሰሎቹ የቅብዓት ተከታዮች ለራሳቸው እምነት እንዲመች አድርገው የጨመሯት ትርጉም ናት ማለት ነው፡፡ ይኸውም “ወልደ አብ” በተባለው መጽሐፋቸው ላይ የጠቀሷትን “በማኅጸነ እግዝእትነ ማርያም በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ከአብ ተወለደ” የምትለዋን አዲስ ፍልስፍናቸውን እውነታ ለማስመሰል የተጠቀሙት የማጭበርበሪያ ዘዴ ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሰዎች ማስረጃ እያሉ በተለያየ ጊዜ የሚጠቅሱትን የጥቅስ ጋጋታ ሁሉ ቅዱሳን አባቶቻችን በየዘመኑ ተነስተው ከጻፉት አንድምታ ጋር በማገናዘብ ስህተታቸው የት ላይ እንዳለ ልናሳውቃቸው ያስፈልጋል፡፡ እኛም እውነት መስሎን በሚጠቅሱት ጥቅስ ምክንያት ተደናግረን ከእውነተኛዋ መንገድ እንዳንወጣ መጠንቀቅ እና መትጋት ያስፈልጋል፡፡ ይቀጥላል

Friday, June 24, 2016

ከኋላ የመጣ ዐይን አወጣ

ከኋላ የመጣ ዐይን አወጣ
በዚህ ርዕስ ለመጻፍ የፈለግሁበት ምክንያት ለብዙ ጊዜ እራሳቸውን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ደብቀው የተለያዩ የክህደት ትምህርቶችን በስውር ሲያስተምሩ የነበሩ የቅባት እምነት ተከታዮች አሁን አሁን ግን "ቀን የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራል" እንዲሉ የተዋህዶን እምነት አስተምህሮ ሲንቁ ሳይ በአደባባይም ላይ አፋቸውን ሞልተው መጽሐፍ ላይ የሌለ ፍልስፍናቸውን እንደ እውነታ በመቁጠር የተወህዶ አርበኞች ተብለው የተጠሩት ቅዱሳን አባቶቻችን የመናፍቃንን ክህደት እና አሽክላ እንዲሁም ወጥመድ ሰባብረው የጣሉበትን ቅዱስ ቃል በተቃራኒው አጣመው በመተርጎም እውነተኛ የሆነችውን ኦርቶዶክስ ተዋህዶን ሲሰድቡ እና ሲያጣጥሉ ስላየሁ ነው። የሚገርማችሁ ነገር አንዱ ሲጠይቅ ምን አለኝ መሰላችሁ "ስለ ተዋህዶ ያስተማረ ሊቅ አለ ወይ? አለኝ ይህንን ብትሰሙ እናንተ ምን እንደምትሉ እንጃ እኔ ግን በጣም ነው የገረመኝ ስለገረመኝም "ከኋላ የመጣ ዐይን አወጣ" ብየ ይህንን ጽሁፍ ለመጻፍ ጀመርኩኝ። በእውኑ ተዋህዶን ሳያነሳ ያስተማረ ሊቅ አለን? አብረን እንየው። በእውነት ሃይማኖተ አበው መጽሐፉን ገዝታችሁ ብታነቡት የተዋህዶን ምስጢር በደንብ በማጉላት ያስተምራል። ሲጀምር "ዘአንገሦ ለስጋ አዳም በመንፈስ ቅዱስ ወረሰዮ ቅዱሰ ወማሕየዌ" ትርጉሙም " በመንፈስ ቅዱስ ሕይዎትነት የአዳምን ባሕርይ ያከበረው የባሕርይ አምላክ ያደረገው እርሱ ነው።" ይህንን ቃል ሃይማኖተ አበው ዘእልመስጦአግያ ምዕራፍ 2÷5 ላይ ይገኛል። ከቁጥር አንድ ጀምሮ ስታነቡት ስለ ትክክለኛይቱ እምነት እንደሚጽፉ ይጠቅስ እና ከዚያ ደግሞ ስለጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት፣ ለሰው ልጆች ድኅነት ሲል ወደዚህ ዓለም መጥቶ መከራን እንደተቀበለ፣ እንደሞተ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ተለይቶ እንደተነሳ ዳግመኛም በዓለም ፍጻሜ ለፍርድ እንደሚመጣ ከጠቀስ በኋላ ይህንን የጻፍኩትን ቃል ይናገረዋል። ቃሉን አንድ በአንድ እንይ። " በመንፈስ ቅዱስ ህይዎትነት የአዳምን ባሕርይ ያከበረው የባሕርይ አምላክ ያደረገው እርሱ ነው።" ከዚህ ቃል እንደምንረዳው "በማኅጸነ እግዝእትነ ማርያም ወልድ ስጋን በነሳ ጊዜ አብ በመንፈስ ቅዱስ አከበረው" የሚለውን የኑፋቄ ትምህርት ሙሉ በሙሉ ውድቅ ያደርገዋል። እነሱ እንደሚሉት "አብ ሥግው ቃልን በመንፈስ ቅዱስ ቢያከብረው" ኖሮ ሊቃውንቱ " በመንፈስ ቅዱስ ህይዎትነት የአዳምን ባሕርይ ያከበረው የባሕርይ አምላክ ያደረገው እርሱ ነው።" ብሎ አይጽፍም ነበር። የአዳምን ባሕርይ ያከበረው የባሕርይ አምላክም ያደረገው እርሱ( ወልድ) ነው ብሎ በግልጽ አማርኛ ተናገረ። ይህ ቃል የሚያረጋግጥልን ሌላ እውነታ አለ ይኸውም በማክበር አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አንድ እንደሆኑ ነው። በዚሁ ምዕራፍ ቁጥር 6 ላይ እንዲህ ይላል። "ዘለብሶ ለአዳም መዋቲ ወአንስኦ ወአዕረጎ እስከ ሰማያት በስጋ ዘሞዖ ለሞት ወአስተኃፈሮ ለዲያብሎስ ዘኮነ ሥሉጠ ወንጉሠ መዋዕለ ነዋኃ" ትርጉም " መዋቲ ስጋን የተዋሃደው ያስነሳው ወደ ሰማይ ያወጣው ሞትን በስጋ ድል የነሳው አምስት ሺ ከአምስት መቶ ዘመን ነግሦ ሠልጥኖ የነበረ ዲያብሎስን ያጠፋው እርሱ ነው።" ቃሉ ሲጀምር ግልጽ በሆነ አማርኛ "መዋቲ ስጋን የተዋሃደው" ይላል። እና ከዚህ በላይ ግልጽ የሆነ ተዋህዶን የሚገልጽ አማርኛ ከየት ይምጣ። ከምዕራፍ 3 ቁጥር 13 ላይ እንዲህ ይላል " ወሥጋ ለብሰ ዘይማስን ዘኢይትረከብ ወኢይማስን ለሥጋ መዋቲ ረሰዮ ዘኢይማስን ወበእንተዝ አስተርአየ በሥጋ መዋቲ አዳም ዘለብሰ አርአያ ዘኢይማስን ዘቦቱ በአርአያ ዘይማስን ሞተ ወፈትሖሙ ለእለ ውስተ ኃጉል በወንጌሉ" ትርጉም "የማይመረመር የማይለወጥ ቃል የሚለወጥ ሥጋን ተዋሕደ መለወጥ ይስማማው የነበረ ሥጋን የማይለወጥ አደረገው ስለዚህም በተወሐደው በመዋቲ አዳም ሥጋ ተገለጠ የማይለወጥ ባሕርይ ያለው ቃል የሚለወጥ ባሕርይ ባለው ሥጋ ሞተ በፍዳ የተያዙትን በወንጌሉ አዳናቸው።" ከዚህ በላይ ለማየት እንደሞከርነው ቅዱሳን አባቶቻችን ርዕትዕት የሆነች እውነተኛዋን ኦረቶዶክስ ተዋህዶ እምነትን አስፍተው አጉልተው አስተምረዋታል ማስተማር ብቻ ሳይሆን በሕይወታቸውም የእምነት ፍሬን በማፍራት ለእኛ ሕያው የሆነ ስራቸውን ትተውልን የባሕርይ አምላክ ብለው ያምኑት ወደ ነበረው ወደ ጌታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ሄደዋል። በዚህ መሰረት ሃይማኖተ አበው መጽሐፉን ከመጀመሪያው ጀምሮ ብታነቡት የተዋህዶን እምነት እውነተኛነት ያስረዳል። ስለዚህ ክፉ መንፈስ የተጠናወታቸው የቅባት እምነት ተከታዮች ሃይማኖተ አበውን ለምንፍቅናቸው ማስረጃ ይሆናል ብለወ መጥቀሳቸው አይገርምም ትላላችሁ? ይባስም ብሎ ቅዱሳን ያስተማሯትን እምነት መንቀፋቸው አያስደንቅም። እንደ እኔ ከሆነ በጣም ያስደንቃል። ስለዚህ በባዶው የሌለ ቃልን እንዳለ እያነበነቡ አንዲትን አረፍተ ነገር ይዞ ከመሮጥ ከመጀመሪያ እስከመጨረሻ በማንበብ፣ ሰዎችን በባዶው እየተሳደቡ እምቡር እምቡር ከማለት ተረጋግቶ ማንበብ እና ምስጢሩን መማር እንዲሁም መመርመር እውነተኛውን መንገድ ለማወቅ እንደሚጠቅማቸው መረዳት አለባቸው። ምዕራፍ 4 ከቁጥር 11 ላይ ደግሞ " መኑ ውእቱ ዝንቱ ዘሐደሶ ለሥጋ እምነ ኃጉል ወተወክፎ እሙስና" ትርጉም "ሥጋን ከብልየቱ ያደሰው ከመለወጥ አድኖ የተዋሐደው ይህ ማን ነው?"ይላል እዚህ ላይ እንግዲህ ምን ይሉ? ነው የእነሱ ሃይማኖተ አበው ይህ ክፍል የለውም? ይህንን ያልኩበት ዋናው ምክንያት በግልጽ ሥጋን ከብልየቱ ያደሰው ይላል በእውነት የሚገርም ድንቅ ቃል ነው ምክንያቱም አካላዊ ቃል በምስጢረ ተዋህዶ ብልየት የነበረበትን ሥጋ በማክበር የእርሱን ባሕርይ ባሕርይ እንደኖረው አድርጎታል። ስለዚህ አብ በመንፈስ ቅዱስ አከበረው የሚለው ቃል ምን ቦታ የለውም ማለት ነው። እዚህ ላይ ደግሞ ሌላው ግልጽ ያልሆነላቸው ነገር መለኮት እና ሥጋ ከመዋሃዳቸው በፊት ሁለት አካል እና ሁለት ባሕርይ መሆናቸውን ነው። ሰለዚህ እኛ ወልድ የተዋሃደውን ሥጋ አከበረው ስንል ከተዋህዶ በፊት ሥጋ እና መለኮት ሁለት አካል እና ሁለት ባሕርይ ስለነበሩ እና በማክበር አብ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ አንድ ስለሆኑ ወልድ ስጋን በተወሃደ ጊዜ የተዋሃደውን ሥጋ አከበረው። ቅዱሳን አባቶቻችን እንዳስተማሩት ከተዋህዶ በኋላስ ሁለትነት ጠፍቶ መለኮት እና ሥጋ በተዋሕዶ አንድ ሆነዋል። አንድ ባሕርይ አንድ አካል በመሆን ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ ሆኗል እንጅ። ሊቃውንቱ ይህን ሲያስረዱ እንዲህ ብለዋል "መኑ ውእቱ ዝንቱ ዘለብሶ ለሰብእ ምድራዊ ውእቱሰ ሰማያዊ ውእቱ" ትርጉም "ምድራዊ ሥጋን የተዋሐደው ይህ ማነው? እርሱ ግን ሰማያዊ ነው" በምዕራፍ 6 ቁጥር 8 ላይም " እግዚአብሔር አብ ለእግዚእነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘተወልደ እምቅድመ ይትፈጠር ዓለም ወልድ ዋሕድ ዘእሩይ ምስሌሁ" ትርጉም " ዓለም ሳይፈጠር የተወለደ የጌታችን የፈጣሪያችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አባቱ እግዚአብሔር አብ አንድ ነው ወልድ ዋህድ ከእርሱ ጋር ትክክል የሚሆን የባሕርይ አምላክ ነው።" እዚህ ላይም ተጽፎ እንደምናየው "ወልድ ዋህድ የባሕርይ አምላክ ነው" አለ እንጅ "ወልድ ቅብዕ" አላለም። ስለዚህ ስህተቱ የት ላይ እንደሆነ መመርመሩ የሕይዎት መንግስትን ለመውረስ ይጠቅማል ማለት ነው። አምላከ ቅዱሳን ማስተዋሉን ያድላቸው

"እርሱ በተዋሕዶ ሰው የሆነ አምላክ ነው" ክፍል 2

በክፍል አንድ ላይ እንዳየነው በተዋሕዶ ከበረ ማለት በተዋሕዶ የመለኮት ገንዘብ ለሥጋ የሥጋ ገንዘብ ደግሞ ለመለኮት ሆነ ማለት ነው። በተዋሕዶ አምላክ ፍጹም ሰው ሆነ ሰውም ፍጹም አማላክ ሆነ ማለት ነው። ከዚህ ውጭ ሌላ ትርጉም የለውም። በራሱ ፍላጎት እና ትርጉም ከዚህ ውጭ ትርጉም አለው የሚል ሰው ካለ እርሱ አባቶቻችን ካስተማሯት እምነት ውጭ ነው ማለት ነው። ይህንን ሲገልጽ ሊቁ ጎርጎርዮስ እንዲህ ብሏል "ወለአስተርእዮቱሂ ለነ በሥጋ ኢይትከሀለነ ናእምሮ ዘከመ ድልወቱ ወበእንተ ዝንቱ ያጌብረነ ንትመሀር እም እሉ መምህራን ዘይቤ ቃል በእንቲአሆሙ ይደሉ ይትወከፉ እምኔሆሙ ኩሎሙ እለ ይሰምዑ ቃለ በእንተ ምሥጢር ዐቢይ ዘለኂሩት" ትርጉሙም "ለእኛም በሥጋ መገለጡን እንደሚገባው መርምረን ልናውቀው አይቻለንም። ጸጋን ለመስጠት ያደረገውን ተዋሕዶ የሚያምኑት ሰዎች ከእነርሱ ትምህርትን ይቀበሉ ዘንድ ይገባል ብሎ ቃል ስለ እነርሱ ከተናገረላቸው ከመምህራን እንማር ዘንድ ያሻናል" ብሏል። ቀጥሎም "ዝንቱ ቃል ዘአስተርአየ በሥጋ በእንቲአነ እንዘ ውእቱ በአርአያ እግዚአብሔር" ትርጉሙም " ይህ እግዚአብሔርን በመልክ የሚመስለው በባሕርይ የሚተካከለው ሲሆን ቃል ስለ እኛ በሥጋ የታየው መታየት ነው" " ወኮነ ምስለ ሰብእ በአርአያ ገብር በሥጋ ዝንቱ ዘአልቦቱ ጥንት ተወክፈ ሎቱ ለባሕቲቱ ህላዌ ሥጋ ዘቦቱ ጥንት ዘነሥአ እም እግዝእትነ ቅድስት ድንግል ማርያም ንጽሕት ዘእንበለ ርስሐት" ትርጉሙም "በተገዥ በአዳም ባሕርይም በሥጋ የሰውነትን ሥራ ሠራ ጥንት የሌለው እርሱ ያለ መለወጥ ንጽሕት ከምትሆን ከቅድስት ድንግል ማርያም የነሣውን ጥንት መገኛ ያለውን የሥጋን ባሕርይ በተለየ አካሉ ተዋሐደ" ሃይማኖተ አበው ዘጎርጎርዮስ ምዕራፍ 35 ቁጥር 10—12 ከጊዜ አንጻር ሁሉን መጥቀስ ስለማይቻል መጽሐፉን ግዙና አንብቡት። አባቶቻችን ያስተማሯት ተወሕዶ እምነት ይህች ናት። አሁን እኛ ቅባቶችን እያልናቸው ያለ "ሥጋ በተዋሕዶ የመለኮትን ገንዘብ ገንዙቡ አድርጎ የባሕርይ አምላክ ከሆነ፣ የአብ ልጅ ከሆነ፣ የአብ ቃል ከሆነ፣ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ ሕይወቱ ከሆነ" ሥጋ እነዚህን የመለኮት ባሕርያት በተዋሕዶ እንዳላገኘ አድርገው "አብ በመንፈስ ቅዱስ ቅብነት ሥጋ የተዋሐደ ቃልን አከበረው ማለት ለምን አስፈለገ? ዋናው ጥያቄ ይህ ነው። እንግዲህ የሚያስተውሉ ከሆነ ይህንን ይመርምሩ እንቢ አሻፈረኝ ብለው ሰውን መሳደብ እና ማጠጣል ከሆነ ግን "ዘቦ እዝን ሰሚዐ ለይስማእ" ብለን ዝም እንላቸዋለን። እኛ ግን እውነታውን ከመናገር እና ከመጻፍ ወደኋላ አንልም። ሦስተኛው ከተዋሕዶ በኋላ ያለው ነው። ከላይም ለመግለጽ እንደሞከርኩት ከተዋሕዶ በኋላ ሁሉትነት ጠፍቶ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ሆኗል የሚለው ነው። በማቴዎስ ወንጌል "ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ዘአፈቅር ዘቦቱ ሠመርኩ" ትርጉሙም "የምወደው በእርሱ ህልው ሆኘ ልመለክ የወደድሁት ልጄ ይህ ነው" አለ ማቴ 3:17
ቀጥሎም እንዲህ አለ "ኢኮነ ዝንቱ አሐዱ ክልኤተ፣ ካልእ ወልድየ ወካልእ ወልደ ማርያም፣ አኮ ካልእ ዘተወልደ በውስተ በአት ወአኮ ካልእ ዘሰገዱ ሎቱ ሰብአ ሰገል አኮ ካልእ ዘተጠምቀ ወአኮ ካልእ ዘኢተጠምቀ አላ ውእቱ ወልድየ ፍቁር ዘቦቱ ሠመርኩ" ትርጉሙም "ይህ አንዱ ሁለት አይደለም ልጄ ያለው ሌላ ከማርያም የተወለደው ሌላ አይደለም። በበረት የተወለደው ሌላ ሰብአ ሰገል የሰገዱለት ሌላ አይደለም። የተጠመቀው ሌላ አይደለም ጥምቀት የማያሻውም ሌላ አይደለም። በእርሱ ህልው ሆኘ ልመለክበት የወደድኩት ልጄ ነው እንጅ" ብሎ ሊቁ በማቴዎስ ወንጌል የተነገረውን ቃል አመስጥሮታል። ( ሃይማኖተ አበው ዘጎርጎርዮስ ምዕራፍ 35 ከቁጥር 14 ጀምሮ ያለውን አንብቡት ) እንግዲህ ተዋሕዶ ማለት ይህች ናት። ከዚህ ውጭ የሆነ ትምሕርት የለም በዚች እምነት ጸንተን እንድንኖር የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት የቅዱሳን መላእክ ተራዳኢነት እና የቅዱሳን አባቶቻችን በረከት እና ጸሎት ይርዳን አሜን።

"እርሱ በተዋሕዶ ሰው የሆነ አምላክ ነው" part 1

"ከመ አሐዱ ውእቱ ባሕቲቱ ውእቱ አምላክ ወሰብእ ኅቡረ" ትርጉሙም "እርሱ በተዋሕዶ ሰው የሆነ አምላክ ነው" ይህንን ቃል የተዋሕዶው ሊቅ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ተናግሮታል። ይህንን እንድጽፍ ያነሳሳኝ ዋናው ነገር ተዋህዶ እና በተዋህዶ ከበረ የሚለው ቃል የተለያየ የሚመስላቸው ብዙ አላዋቂ የሆኑ የቅባት እምነት ተከታዮች ስላሉ ነው። በተዋህዶ ከበረ ሲባል ቃል እና ሥጋ ከተዋሐዱ በኋላ እንደገና ተከፍሎ ቃል ሥጋን አከበረው ማለት የሚመስላቸው ብዙ ምስጢሩ ያልገባቸው፣ቅዱሳን አባቶቻችን የጻፏቸውን ምስጢራት ሲጠቅሱላቸው እውነታውን በመረዳት ፋንታ አፋቸውን ለስድብ የሚከፍቱ፣ እራሳቸውን ብዙ መጻሕፍትን እንዳወቁና ብዙ ምስጢራትን እንደመረመሩ አድርገው የሚያስቡ በተግባር የሚታይ ፍሬያቸው ግን በተቃራኒው የሆነ ብዙ ቅባቶች ሥላሉ እነሱ ይህን እውነታ ይረዱ ዘንድ ቅዱሳን አባቶቻችን በመጻሕፍት ሥለ ተዋሕዶ የተናገሩትን በመጥቀስ መጻፍ እጀምራለሁ። በመጀመሪያ እንዲረዱት የምፈልገው ነገር ተዋሕዶ እና በተዋሕዶ ከበረ የሚሉት ቃላት ትርጉማቸው አንድ እንደሆነ ነው። የተለያየ ትርጉም የላቸውም ሊኖራቸውም አይችልም። አሁን ሊቁ ወደ ተናገረው ቃል ልመለስ " ከመ አሐዱ ውእቱ ባሕቲቱ ውእቱ አምላክ ወሰብእ ኅቡረ" ትርጉሙም " እርሱ በተዋሕዶ ሰው የሆነ አምላክ ነው" ይላል እዚህ ላይ የምንረዳው ግልጽ የሆነ የተዋሕዶን ምስጢር ነው። ተዋሕዶ ምንድን ነው? የሚለውን እንይ ተዋሕዶ የሚለውን በ 3 ከፍለን እንየው እነዚህም ቅድመ ተዋሕዶ፣ ጊዜ ተዋሕዶና ድኅረ ተዋሕዶ ናቸው። በመጀመሪያ ቅድመ ተዋሕዶን ስናይ:— ቅድመ ተዋህዶ ሁለት አካል እና ሁለት ባሕርይ ነው ያሉት ማለትም መለኮታዊ አካል እና ሥጋዊ አካል፣ መለኮታዊ ባሕርይ እና ሥጋዊ ባሕርይ ናቸው። እንግዲህ እዚህ ላይ ልናስተውለው የሚገባ ነገር ቅድመ ተዋሕዶ አንድ ናቸው ማለት እንደማይገባ ነው። ሁለተኛው ደግሞ ጊዜ ተዋሕዶ ነው። በዚህ ጊዜ ደግሞ መለኮታዊ አካል ከሥጋዊ አካል፣ መለኮታዊ ባሕርይ ከሥጋዊ ባሕርይ አንድ የሆኑበት ምሥጢር ነው። ይህም ማለት መለኮታዊ አካል ሥጋዊ አካልን ሳያጠፋ እንዲሁም መለኮታዊ ባሕርይ ሥጋዊ ባሕርይን ሳያጠፋ፣ ሥጋዊ አካልም መለኮታዊ አካልን ሳያጠፋ እንዲሁም ሥጋዊ ባሕርይ መለኮታዊ ባሕርይን ሳያጠፋ በተዐቅቦ በመጠባበቅ፣ ያለ መለወጥ፣ ያለ ኅድረት፣ ያለመመለስ፣ ያለመቀላቀል፣ ያለመለያየት መለከታዊ አካል ከሥጋዊ አካል፣ መለኮታዊ ባሕርይ ከሥጋዊ ባሕርይ ፍጹም አንድ የሆኑበት ምሥጢር ነው። ለዚህም ነው ሊቁ ጎርጎርዮስ " ከመ አሐዱ ውእቱ ባሕቲቱ ውእቱ አምላክ ወሰብእ ኅቡረ" ትርጉሙም " እርሱ በተዋሕዶ ሰው የሆነ አምላክ ነው" ሃይማኖተ አበው ዘጎርጎርዮስ 35 ቁጥር 21ብሎ የተናገረዉ። በዚሁ ምዕራፍ ቁጥር 2 ላይ እንዲህ ይላል " እስመ ክርስቶስ ኢ ፍጡር ወፍጡር ኀብሩ በአሐዱ ህላዌ ወአካል" ትርጉሙም "ክርስቶስ ማለት ፈጣሪና ፍጡር አንድ አካል አንድ ባሕርይ በመሆን አንድ ሆነ ማለት ነው።" ሌላው እዚህ ላይ የምናየው ነገር በተዋሕዶ የመለኮት ገንዘብ ለሥጋ የሥጋ ገንዘብ ለመለኮት መሆኑን ነው። የመለኮት ገንዘብ ምን ምን ናቸው ቢሉ አምላክነት፣ ፈጣሪነት፣ ሁሉን ቻይነት፣ የአብ ልጅ መባል፣ ቃለ አብ መባል፣ ረቂቅነት፣ አለመራብ፣ አለመጠማት፣ ይህን የመሰሉት ሁሉ ናቸው። የሥጋ ገንዘብ የሚባሉት ደግሞ ፍጡርነት፣ መራብ፣ መጠማት፣ ግዙፍነት፣ ውሱንነት፣ ደካማነት፣ ሕማም የሚስማማው፣ ሞት የሚስማማው እና የመሳሰሉት ናቸው። እንግዲህ ዋናው ምሥጢር እዚህ ላይ ነው። በተዋሕዶ ሥጋ የመለኮትን ገንዘብ ገንዘብ አደረገ ማለት ሥጋ የአብ ልጅ መባልን፣ ቃለ አብ መባልን፣ ፈጣሪነትን፣ ሁሉን ቻይነትን፣ የማይመረመር መሆንን ገንዘቡ አደረገ ማለት ነው። መለኮት ደግሞ ከላይ የጠቀስኳቸውን የሥጋ ገንዘቦች ገንዘብ አደረገ እንላለን። ይህንን ስንል ግን የሥጋ ኃጢአት ወደ መለኮት አልተላለፈበትም። ከዚህ ላይ እንደጠቀስኩት በተዋሕዶ ሥጋ አምላክነትን ወልደ አብነትን፣ ቃለ አብነትን ገንዘቡ ካደረገ ከዚህ ሌላ ምንም ምን ተጨማሪ ነገር አያስፈልግም ማለትም ከዚህ በኋላ ቅባቶች እንደሚሉት በመንፈስ ቅዱስ ቅባትነት አብ ሥጋን የተዋሃደ መለኮትን አከበረው አይባልም ይሕ ፈጽሞ ክህደት ነው ምክንያቱም መጀመሪያ በተዋህዶ ሥጋ የቃልን ገንዘብ ገንዘቡ አድርጓልና ነው። እንግዲህ በተዋህዶ ሥጋ የቃልን ገንዘብ ገንዘቡ ካደረገ መለኮተን የተዋሃደ ሥጋ በአብ ልብነት ያስባል፣ በመንፈስ ቅዱስ ሕይዎትነት ከዚህ እስከዚህ ተብሎ ለማይነገር ዘመን ለዘላለሙ ሕያው ሆኖ ይኖራል ማለት ነው። ለዚህም ነው ቅዱስ ጎርጎርዮስ "ወዓዲመ ይትበሀል ፍጡረ በእንተ ዘኮነ ሥጋ ወኀደረ ላዕሌነ ዝንቱ ሶበ ኮነ ሥጋ ከሠተ ስብሐቲሁ በምግባር ከመ እግዚአብሔር አስተርአየ በሥጋ ወውእቱ አምላክ ወልድ ዋሕድ ዘሀሎ ውስተ ሕፅነ አቡሁ" ትርጉሙም " ዳግመኛም ባሕርያችንን ተዋሕዶ ሰው ስለሆነ ሰው ይባላል እርሱ ሰው በሆነ ጊዜ እግዚአብሔር በሥጋ እንደታየ በሥራው ጌትነቱን ገለጠ እርሱ አምላክ ወልድ ዋሕድ በአባቱ ዕሪና ያለ ነው" ብሎ የተናገረው ሥለዚህ በተወህዶ ከበረ ማለት ቅባቶች እንደሚሉት ከተዋሕዶ በኋላ መለኮትና ሥጋ ተለያይተው መለኮት ሥጋን አከበረ ማለት አይደለም ሊሆንም አይችልም። ቅዱሳን አባቶቻችንም እንደዚህ አላሉም የእነሱን አሰረ ፍኖት የምንከተል እኛ የተዋሕዶ ልጆችም አላልንም ወደፊትም አንልም። ይቀጥላል•••

Thursday, June 23, 2016

ማስረጃ ወይስ ሰውን መሸወጃ ክፍል አራት



“ወአርአየ ከመ ወልደ እግዚአብሔር ውእቱ በኃይሉ ወበመንፈሱ“ የሚለው ቃል ”መለኮት ሰው ቢሆን በማኅጸነ እግዝእትነ ማርያም በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ከአብ የተወለደውን ልደት ሲናገር ነው“፡፡ የሚል ትርጉም የለውም፡፡
ስለዚህ አዲሱ እና መሰሎቹ የቅባት እምነት ተከታዮች በሚመቻቸው መልኩ መተርጎምና ሰዎችን ማወናበድ ጀምረዋል ማለት ነው፡፡ እንዲህ ከሆነ ደግሞ ጌታችን  ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረው ቃል ማለትም “ይቀልል ኅልፈተ ሰማይ ወምድር እምትደቅ አሃቲ ቃል እም ኦሪት ወእም ነቢያት” ትርጉሙም “ከኦሪት እና ከነቢያት አንዲት ቃል ከምትወድቅ የሰማይ እና የምድር ማለፍ ይቀላል” የሚለው ቃል ተሸሯል ማለት ነው፡፡ አምላካችን ይህንን ቃል የተናገረው እንመራበትም ዘንድ በመጻሕፍት በቅዱሳን ላይ አድሮ ያጻፈው ህጉን አክብረን እንድንጠቀም ነው፡፡ በክፍል አንድ ላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት የቅብዓት እምነት ተከታዮች  ”መለኮት ሰው ቢሆን በማኅጸነ እግዝእትነ ማርያም በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ከአብ ተወለደየምትለዋን የክህደት ፍልስፍና  እና የጨለማመንገድ እንደ እውነታ አስመስሎ በማቅረብ እውነታውን ያልተረዱ የዉኃንን ለማደናገር ነው ማለት ነው፡፡ በአጠቃላይ በዚህ አይነት በተሳሳተ መንገድ እየተረጎሙ ለሌሎች መሰናክል ከመሆን እውነታውን ተረድቶ ወደ እውነተኛዋ መንገድ መመለስ ጥሩ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ እንደ ሳጥናኤል አሻፈረኝ ቢሉ መጨሻው ውርደት እና ሞት ነው፡፡ ስለዚህ በማስተዋል ቅዱሳን አባቶቻችን ያስተማሯትን ከዚያም አልፎ ሕይዎታቸውን ለስጋ ሞት አሳልፎ እስከ መስጠት ድረስ የታመኑላትን እምነት አጽንተን መከተል ያስፈልጋል፡፡ አምላከ ቅዱሳን በክህደት መንገድ ለተጠመዱት ማስተዋሉን ያድልልን!!!

ማስረጃ ወይስ ሰውን መሸወጃ (ክፍል ሦስት)



በክፍል ሁለት መዝሙር 2÷7 ያለውን አይተናል፡፡ በዚህ ክፍል ደግሞ ሮሜ 1÷2-4 ያለውን እናለን፡፡ እዚህ ላይም እንድትረዱት የምፈልገው ነገር እነ አዲሱ እና መሰሎቻቸው አባቲቻችን በመንፈስ ቅዱስ የተረጎሙትን እነሱ ግን  ምንም ሳይገባቸው እና ምስጢሩን ሳይረዱ አዋቂ ለመባል ብቻ በራሳቸው መንገድ እየተረጎሙ እንደ ማስረጃ ብለው የሚያቀርቡት መሆኑን እንድትረዱ እና እውነታውን እንድታውቁት  ነው፡፡ ለዚያም ያመቸኝ ዘንድ ነው አንድምታው ላይ ያለውን ምንም ሳልጨምር ሳልቀንስ የምጽፍላችሁ፡፡
በመጀመሪያ አዲሱ  እና ተከታዮቹ የተረጎሙትን አቀርብላችሁና ቀጥሎ ደግሞ  የቤተክርስቲያን ሊቃውንት አባቶቻችን ተርጉመው ካስቀመጡት አንድምታ ትርጓሜ ላይ ያለውን ቃል ሙሉ በሙሉ አቀርብላችኋለሁ፡፡
መልካም ንባብ
ሮሜ 1÷2-4 ”በእንተ ወልዱ ዘተወልደ ወመጽአ እም ዘርአ ዳዊት በስጋ ሰብእ ወአርአየ ከመ ወልደ እግዚአብሔር ውእቱ በኃይሉ ወበመንፈሱ ቅዱስ“ አቶ አዲሱ እና ተከታዮቹ ሲተረጉሙት እንዲህ ይሉታል፡፡
”በእንተ ወልዱ ዘተወልደ“ ማለቱ  እምቅድመ ዓለም በመለኮቱ  ከአብ የተወለደውን ልደት ሲናገር ነው፡፡
“ወአርአየ ከመ ወልደ እግዚአብሔር ውእቱ በኃይሉ ወበመንፈሱ“ ማለቱ መለኮት ሰው ቢሆን በማኅጸነ እግዝእትነ ማርያም በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ከአብ የተወለደውን ልደት ሲናገር ነው፡፡
“ወመጽአ እም ዘርአ ዳዊት በስጋ ሰብእ” ማለቱ ደግሞ ከእግዝእትነ ማርያም በስጋ መወለዱን ሲናገር ነው ብሎ ተርጉሞታል፡፡
ከዚህ ቀጥለን ደግሞ አንድምታ መጽሐፉ ላየረ ያለውን ትርጉም እንመልከት
መጽሐፉ ሲጀምር እንዲህ ይላል፡- ”ዘአቅደመ ነጊረ በአፈ ነቢያቲሁ ቅዱሳት በእንተ ወልዱ ዘተወልደ” ትርጉሙም፡- አካል ዘእም አካል፣ ባሕርይ ዘእም ባሕርይ የተወለደ የልጁን ነገር ፤ ስለ ተወለደ ስለ ልጁ፤ በዳዊት፡- ”ወልድየ አንተ ወአነ ዮም ወለድኩከ“መዝ 2÷7፤ በነገስት፡- “አነ እከውኖ አባሁ ወውእቱ ይከውነኒ ወልድየ” 2ኛ ነገ 7÷14፤ በሰሎሞን፡- ”እምቅድመ አድባር ወአውግር ወለደኒ“ ምሳሌ 8÷25፤ በነቢያት በመጻሕፍት  ያናገረ የአብን ነገር ከማስተምር ከእኔ ከጳውሎስ የተገኘች ክታብ (መልእክት)
ሐተታ ፡- መጻሕፍት፣ ነቢያት የሚሏቸው ልዩ ናቸውን ቢሉ ፡-
ነቢያት ያላቸው ሳሉ የተናገሩት፡፡ መጻሕፍት የሚላቸው ከሞቱ በኋላ የተጻፉት ናቸው፡፡ ይህማ ሳሉ የተናገሩት ከሞቱ በኋላ ቢጻፍ ልዩ ነውን ብሎ ነቢያት የሚላቸው አድሮ ያናገራቸው፡፡ መጻሕፍት የሚላቸው በዘፈቀደ ታይቶ ያጻፋቸው ናቸው፡፡ ቅዱሳት ንጹሐት ክቡራት ሲል ነው፡፡ ርኩሳት መጻሕፍተ ጥንቆላ አሉና ከዚያ ሲለይ ንጹሐት አለ፡፡
ምኑናት መጻሕፍተ ደብዳቤ አሉና ከዚያ ሲለይ ክቡራት አለ፡፡
“ወመጽአ እም ዘርዐ ዳዊት በስጋ ሰብእ ” ትርጉሙም፡- በስጋ ከዘርዐ ዳዊት ስለተወለደ ስለ ልጁ፤ የተወለደ የልጁን ነገር በኢሳይያስ ” ትወጽእ በትር እምስርዎ እሴይ  ወየዐርግ  ጽጌ እምጉንዱ””ወይቀውም ሥርዎ እሴይ ወዘተወልደ እምኔሁ ይከውን ንጉሠ ለአሕዛብ“ ኢሳ 11÷1 እና 10፤ በዳዊት “ እስመ እምፍሬ ከርስከ አነብር ዲበ መንበርከ ” መዝ 132÷1 ብሎ በነቢያት በመጻሕፍት ያናገረ የአብን ህግ ከማስተምር ከእኔ ከጳውሎስ
ሐተታ፡- ሥጋ እንስሳ አለና ከዚያ ሲለይ ስጋ ሰብእ አለ፡፡ ምነው ዘርዐ ዳዊት ያለው አይበቃምን ቢሉ ነፍስን እንደነሳ ለማጠየቅ ፤ ያውስ ቢሆን ”ዘርዐ አብርሐም አልዐለ“ እንዲል(ዮሐንስ አፈወርቅ) ዘርዐ ዳዊት ያለው አይበቃምን ቢሉ  በከዊን ሲል ነው፡፡ ”ወአርአየ ከመ ወልደ እግዚአብሔር በኃይሉ ወበመንፈሱ ቅዱስ” ትርጉሙም ፡- ”ዘተወልደ ወዘአርአየ “ ብሎ ለወልድ ይቀጽላል፡፡ ኃይሉ ሕይዎቱ በሚሆን በመንፈስ ቅዱስ ከዘርዐ ዳዊት በመወለዱ ወልደ እግዚአብሔር እንደሆነ ስላሳየ ፣ ስለ ልጁ ያሳየ፣ የልጁን ሕግ ወንጌልን ከማስተምር ከእኔ ከጳውሎስ
ሐተታ፡- አምስት ሽህ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም ከእመቤታችን ያለ አባት መወለዱ ቅድመ ዓለም ከአብ ያለ እናት መወለዱን ያስረዳልና፡፡ “ልደት ቀዳማዊ ተዐውቀ በደኃራዊ ልደት”  እንዲል (ሃይማኖተ አበው ሱኑት)
አንድም፡ በኃይሉ፡- በኅቱም ድንግልና ተጸንሶ በኅቱም ድንግልና በመወለዱ ፡፡ ወበመንፈሱ ቅዱስ ፡- መንፈስ ቅዱስን በዮርዳኖስ በርግብ አምሳል በእራሱ ላይ በማኖሩ ፡፡”አሜሃ ስምዐ ኮነ መንፈስ በዮርዳኖስ ከመ ወልድ ዘበአማን ወአምላ ዘበአማን“ እንዲል ቄርሎስ
አንድም፡ በኃይሉ፡- 3 አመት 3 ወር ባደረገው ተአምራት፡፡
ወበመንፈሱ ቅዱስ፡- መንፈስ ቅዱስን ለሐዋርያት በጽርሐ ጽዮን በመስደዱ ፡፡
አንድም፡ “ዘአቅደመ ወዘአርአየ” ብሎ ለአብ ይቀጽላል፡፡ ”በኃይሉ ከመ ወልደ እግዚአብሔር አርአየ በመንፈስ ቅዱስ“ ሲተረጎም፡ በባሕርዩ ወልደ እግዚአብሔር እንደሆነ መንፈስ ቅዱስን በእራሱ ላይ በማኖር ያሳየ የልጁን ነገር፡፡
 አንድም ፡ “በመንፈስ ቅዱስ ከመ ወልደ እግዚአብሔር አርአየ በኃይሉ” በግብረ መንፈስ ቅዱስ በመወለዱ ወልደ እግዚአብሔር እንደሆነ በግብሩ፣ በነገሩ አሳየ አለ፡፡  በነገሩ፡- ”ዝንቱ ውእቱ ወልድየ“ ብሎ፡፡ በግብሩ፡- መንፈስ ቅዱስን በርግብ አምሳል በእራሱ ላይ በማኖሩ ያሳይ የልጁን ነገር በኢሳይያስ “ቁልዔየ ፍቁርየ ዘሰምረቶ ነፍስየ ወአነብር መንፈስየ ላዕሌሁ ”ኢሳ 11፡2
ከዚህ በላይ ቤተክርስቲያን ከምትጠቀምበት የአንድምታ ትርጓሜ መጽሐፍ ያለውን ቃል ሙሉ ትርጉሙን  እንዳየነው