
በአንድ አካባቢ ባማረና በተዋበ ግቢ የምትኖር
አንድ ኤሊ ነበረች፡፡ በዚያው አካባቢ በምድረ በዳ የምትኖር አንዲት ጥንቸል ነበረች፡፡ ይህች ጥንቸል ማለፊያ መንገዷ በኤሊዋ መኖሪያ
አጠገብ ስለነበር ጠዋት ማታ ስትመላለስ ኤሊዋን እያየች እጅግ ትቀናና እንዴት እንደምታስወጣት እና እርሷ ከዚያ ቦታ እንደምትገባ
ታስብ ነበር፡፡ በዚህ ሃሳብ እየኖረች እያለ አንድ ቀን ልዩ ሃሳብ መጣላት፡፡ ይሄውም ውድድር መወዳደር ነው፡፡ ጥንቸሏ ይህን ሃሳብ
ያሰበችው ኤሊዋን በሩጫ ውድድር እንደምትቀድማት ስላሰበች ነው፡፡ ይህን ሃሳብ ይዛ ወደ ኤሊዋ ሄደችና ነገረቻት እንዲሁም በውድድሩ
የተሸነፈ ባማረና በተዋበው ግቢ ሊኖር እንደሚገባ አስረዳቻት፡፡ ኤሊዋም በሃሳቡ ተስማማችና የውድድሩን ቀን ቆርጠው ተለያዩ፡፡ የውድድሩ
ቀን በደረሰ ጊዜ ሁለቱም በቦታው ተገኝተው ውድድሩ ተጀመረ፡፡ እንደተጀመረም ጥንቸሏ እንደ ሚስያል ተወንጭፋ ኤሊዋን ቀድማት ሄደችና
ዞራ ስታይ ኤሊዋ ያለችበት ቦታ አይታይም፡፡ በዚህም ጊዜ ኤሊዋ በኔ መድረስ ስለማትችል ትንሽ ልተኛ ብላ እንቅልፏን ለጥ አለች፡፡
ኤሊዋም ተስፋ ሳትቆርጥ በጥንቸሏ ለመድረስ ትሮጥ ነበር፡፡ በዚህም ጊዜ ጥንቸሏ ተኝታ ስለነበር ኤሊዋ ቀድማ በመግባት ውድድሩነ
በድል አጠናቀቀች፡፡ ጥንቸሏ ከእንቅልፏ ስትነቃ በኤሊ እንደተሸነፈች ተረዳች፡፡ በአሁኑ ወቅትም ብዙ ሰዎች እንደ ጥንቸል በሌሎች
መልካም ኑሮ የሚቀኑ አሉ፡፡ የጥንቸል ፍላጎት ኤሊዋ ከምትኖርበት የተደላደለ ህይዎት ማሰወጣት ነበር፡፡ ዛሬ ዛሬ እንደ ጥንቸል
አይነት ብዙ ሰዎች ሌሎች በልተው ስላደሩ፣ ልብስ ስለለበሱ፣ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ስላገኙ እና ጥሩ በሆነ የቤተሰብ አኗኗር ስለኖሩ
ብቻ በቅናት መንፈስ ተነሳስተው ሰዎችን ወደ ጥልቅ የዉድቀት ጉድጓድ ለመጣልና ህይዎታቸውን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት የሚሮጡ ሆነዋል፡፡
ሆኖም ግን በሌሎች ተንኮልና የቅናት መንፈስ ሳይጨነቁ እንደ ኤሊ ተስፋ ሳይቆርጡ ስራቸውን በትግስት የሚሰሩ ሰዎች በሰዎች ዘንድ
የተጠሉ ቢሆንም እና እስከ ሞት ድረስ የሚያደርስ መከራ ቢገጥማቸውም ሁሉን በጸጋና በትግስት ከተቀበሉት ፍጻሜያቸው ያምራል፡፡ ኤሊዋ
ጥንቸሏን በመቅደም እነዳሳፈረቻት ሁሉ እንደ እሷ አይነት ሰዎችም ተስፋ ሳይቆርጡ በህይዎታቸው ተግተው የሚኖሩ ከሆነ ፈተናውን ሁሉ
አልፈው ሲቀኑባቸው የነበሩ ሰዎችን አፍ ማስያዝና የድል አክሊልን መቀዳጀት ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ተስፋ ሳንቆርጥ ስራችንን በመስራት
በአገራችን ላይ ያሉ ሳይሰሩ ነገር በማመላለስ ብቻ በሰው ጫንቃ ላይ ተቀምጠው የችግረኞችን እድል ወደ ራሳቸው በማጠፍ የሰው ደም
እየጠጡ የሚኖሩ ሰዎችን እውነታውን በመግለጽ ልናሳፍራቸው ያስፈልጋል፡፡
መጀመሪያ ግን ራሳችንን ለመፈተሽ ያህል ስንቶች ነን እንደ ጥንቸሏ
ሆነን የምንኖር? እንደ ኤሊዋስ?
ይቀጥላል....



