Friday, June 24, 2016

ከኋላ የመጣ ዐይን አወጣ

ከኋላ የመጣ ዐይን አወጣ
በዚህ ርዕስ ለመጻፍ የፈለግሁበት ምክንያት ለብዙ ጊዜ እራሳቸውን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ደብቀው የተለያዩ የክህደት ትምህርቶችን በስውር ሲያስተምሩ የነበሩ የቅባት እምነት ተከታዮች አሁን አሁን ግን "ቀን የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራል" እንዲሉ የተዋህዶን እምነት አስተምህሮ ሲንቁ ሳይ በአደባባይም ላይ አፋቸውን ሞልተው መጽሐፍ ላይ የሌለ ፍልስፍናቸውን እንደ እውነታ በመቁጠር የተወህዶ አርበኞች ተብለው የተጠሩት ቅዱሳን አባቶቻችን የመናፍቃንን ክህደት እና አሽክላ እንዲሁም ወጥመድ ሰባብረው የጣሉበትን ቅዱስ ቃል በተቃራኒው አጣመው በመተርጎም እውነተኛ የሆነችውን ኦርቶዶክስ ተዋህዶን ሲሰድቡ እና ሲያጣጥሉ ስላየሁ ነው። የሚገርማችሁ ነገር አንዱ ሲጠይቅ ምን አለኝ መሰላችሁ "ስለ ተዋህዶ ያስተማረ ሊቅ አለ ወይ? አለኝ ይህንን ብትሰሙ እናንተ ምን እንደምትሉ እንጃ እኔ ግን በጣም ነው የገረመኝ ስለገረመኝም "ከኋላ የመጣ ዐይን አወጣ" ብየ ይህንን ጽሁፍ ለመጻፍ ጀመርኩኝ። በእውኑ ተዋህዶን ሳያነሳ ያስተማረ ሊቅ አለን? አብረን እንየው። በእውነት ሃይማኖተ አበው መጽሐፉን ገዝታችሁ ብታነቡት የተዋህዶን ምስጢር በደንብ በማጉላት ያስተምራል። ሲጀምር "ዘአንገሦ ለስጋ አዳም በመንፈስ ቅዱስ ወረሰዮ ቅዱሰ ወማሕየዌ" ትርጉሙም " በመንፈስ ቅዱስ ሕይዎትነት የአዳምን ባሕርይ ያከበረው የባሕርይ አምላክ ያደረገው እርሱ ነው።" ይህንን ቃል ሃይማኖተ አበው ዘእልመስጦአግያ ምዕራፍ 2÷5 ላይ ይገኛል። ከቁጥር አንድ ጀምሮ ስታነቡት ስለ ትክክለኛይቱ እምነት እንደሚጽፉ ይጠቅስ እና ከዚያ ደግሞ ስለጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት፣ ለሰው ልጆች ድኅነት ሲል ወደዚህ ዓለም መጥቶ መከራን እንደተቀበለ፣ እንደሞተ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ተለይቶ እንደተነሳ ዳግመኛም በዓለም ፍጻሜ ለፍርድ እንደሚመጣ ከጠቀስ በኋላ ይህንን የጻፍኩትን ቃል ይናገረዋል። ቃሉን አንድ በአንድ እንይ። " በመንፈስ ቅዱስ ህይዎትነት የአዳምን ባሕርይ ያከበረው የባሕርይ አምላክ ያደረገው እርሱ ነው።" ከዚህ ቃል እንደምንረዳው "በማኅጸነ እግዝእትነ ማርያም ወልድ ስጋን በነሳ ጊዜ አብ በመንፈስ ቅዱስ አከበረው" የሚለውን የኑፋቄ ትምህርት ሙሉ በሙሉ ውድቅ ያደርገዋል። እነሱ እንደሚሉት "አብ ሥግው ቃልን በመንፈስ ቅዱስ ቢያከብረው" ኖሮ ሊቃውንቱ " በመንፈስ ቅዱስ ህይዎትነት የአዳምን ባሕርይ ያከበረው የባሕርይ አምላክ ያደረገው እርሱ ነው።" ብሎ አይጽፍም ነበር። የአዳምን ባሕርይ ያከበረው የባሕርይ አምላክም ያደረገው እርሱ( ወልድ) ነው ብሎ በግልጽ አማርኛ ተናገረ። ይህ ቃል የሚያረጋግጥልን ሌላ እውነታ አለ ይኸውም በማክበር አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አንድ እንደሆኑ ነው። በዚሁ ምዕራፍ ቁጥር 6 ላይ እንዲህ ይላል። "ዘለብሶ ለአዳም መዋቲ ወአንስኦ ወአዕረጎ እስከ ሰማያት በስጋ ዘሞዖ ለሞት ወአስተኃፈሮ ለዲያብሎስ ዘኮነ ሥሉጠ ወንጉሠ መዋዕለ ነዋኃ" ትርጉም " መዋቲ ስጋን የተዋሃደው ያስነሳው ወደ ሰማይ ያወጣው ሞትን በስጋ ድል የነሳው አምስት ሺ ከአምስት መቶ ዘመን ነግሦ ሠልጥኖ የነበረ ዲያብሎስን ያጠፋው እርሱ ነው።" ቃሉ ሲጀምር ግልጽ በሆነ አማርኛ "መዋቲ ስጋን የተዋሃደው" ይላል። እና ከዚህ በላይ ግልጽ የሆነ ተዋህዶን የሚገልጽ አማርኛ ከየት ይምጣ። ከምዕራፍ 3 ቁጥር 13 ላይ እንዲህ ይላል " ወሥጋ ለብሰ ዘይማስን ዘኢይትረከብ ወኢይማስን ለሥጋ መዋቲ ረሰዮ ዘኢይማስን ወበእንተዝ አስተርአየ በሥጋ መዋቲ አዳም ዘለብሰ አርአያ ዘኢይማስን ዘቦቱ በአርአያ ዘይማስን ሞተ ወፈትሖሙ ለእለ ውስተ ኃጉል በወንጌሉ" ትርጉም "የማይመረመር የማይለወጥ ቃል የሚለወጥ ሥጋን ተዋሕደ መለወጥ ይስማማው የነበረ ሥጋን የማይለወጥ አደረገው ስለዚህም በተወሐደው በመዋቲ አዳም ሥጋ ተገለጠ የማይለወጥ ባሕርይ ያለው ቃል የሚለወጥ ባሕርይ ባለው ሥጋ ሞተ በፍዳ የተያዙትን በወንጌሉ አዳናቸው።" ከዚህ በላይ ለማየት እንደሞከርነው ቅዱሳን አባቶቻችን ርዕትዕት የሆነች እውነተኛዋን ኦረቶዶክስ ተዋህዶ እምነትን አስፍተው አጉልተው አስተምረዋታል ማስተማር ብቻ ሳይሆን በሕይወታቸውም የእምነት ፍሬን በማፍራት ለእኛ ሕያው የሆነ ስራቸውን ትተውልን የባሕርይ አምላክ ብለው ያምኑት ወደ ነበረው ወደ ጌታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ሄደዋል። በዚህ መሰረት ሃይማኖተ አበው መጽሐፉን ከመጀመሪያው ጀምሮ ብታነቡት የተዋህዶን እምነት እውነተኛነት ያስረዳል። ስለዚህ ክፉ መንፈስ የተጠናወታቸው የቅባት እምነት ተከታዮች ሃይማኖተ አበውን ለምንፍቅናቸው ማስረጃ ይሆናል ብለወ መጥቀሳቸው አይገርምም ትላላችሁ? ይባስም ብሎ ቅዱሳን ያስተማሯትን እምነት መንቀፋቸው አያስደንቅም። እንደ እኔ ከሆነ በጣም ያስደንቃል። ስለዚህ በባዶው የሌለ ቃልን እንዳለ እያነበነቡ አንዲትን አረፍተ ነገር ይዞ ከመሮጥ ከመጀመሪያ እስከመጨረሻ በማንበብ፣ ሰዎችን በባዶው እየተሳደቡ እምቡር እምቡር ከማለት ተረጋግቶ ማንበብ እና ምስጢሩን መማር እንዲሁም መመርመር እውነተኛውን መንገድ ለማወቅ እንደሚጠቅማቸው መረዳት አለባቸው። ምዕራፍ 4 ከቁጥር 11 ላይ ደግሞ " መኑ ውእቱ ዝንቱ ዘሐደሶ ለሥጋ እምነ ኃጉል ወተወክፎ እሙስና" ትርጉም "ሥጋን ከብልየቱ ያደሰው ከመለወጥ አድኖ የተዋሐደው ይህ ማን ነው?"ይላል እዚህ ላይ እንግዲህ ምን ይሉ? ነው የእነሱ ሃይማኖተ አበው ይህ ክፍል የለውም? ይህንን ያልኩበት ዋናው ምክንያት በግልጽ ሥጋን ከብልየቱ ያደሰው ይላል በእውነት የሚገርም ድንቅ ቃል ነው ምክንያቱም አካላዊ ቃል በምስጢረ ተዋህዶ ብልየት የነበረበትን ሥጋ በማክበር የእርሱን ባሕርይ ባሕርይ እንደኖረው አድርጎታል። ስለዚህ አብ በመንፈስ ቅዱስ አከበረው የሚለው ቃል ምን ቦታ የለውም ማለት ነው። እዚህ ላይ ደግሞ ሌላው ግልጽ ያልሆነላቸው ነገር መለኮት እና ሥጋ ከመዋሃዳቸው በፊት ሁለት አካል እና ሁለት ባሕርይ መሆናቸውን ነው። ሰለዚህ እኛ ወልድ የተዋሃደውን ሥጋ አከበረው ስንል ከተዋህዶ በፊት ሥጋ እና መለኮት ሁለት አካል እና ሁለት ባሕርይ ስለነበሩ እና በማክበር አብ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ አንድ ስለሆኑ ወልድ ስጋን በተወሃደ ጊዜ የተዋሃደውን ሥጋ አከበረው። ቅዱሳን አባቶቻችን እንዳስተማሩት ከተዋህዶ በኋላስ ሁለትነት ጠፍቶ መለኮት እና ሥጋ በተዋሕዶ አንድ ሆነዋል። አንድ ባሕርይ አንድ አካል በመሆን ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ ሆኗል እንጅ። ሊቃውንቱ ይህን ሲያስረዱ እንዲህ ብለዋል "መኑ ውእቱ ዝንቱ ዘለብሶ ለሰብእ ምድራዊ ውእቱሰ ሰማያዊ ውእቱ" ትርጉም "ምድራዊ ሥጋን የተዋሐደው ይህ ማነው? እርሱ ግን ሰማያዊ ነው" በምዕራፍ 6 ቁጥር 8 ላይም " እግዚአብሔር አብ ለእግዚእነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘተወልደ እምቅድመ ይትፈጠር ዓለም ወልድ ዋሕድ ዘእሩይ ምስሌሁ" ትርጉም " ዓለም ሳይፈጠር የተወለደ የጌታችን የፈጣሪያችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አባቱ እግዚአብሔር አብ አንድ ነው ወልድ ዋህድ ከእርሱ ጋር ትክክል የሚሆን የባሕርይ አምላክ ነው።" እዚህ ላይም ተጽፎ እንደምናየው "ወልድ ዋህድ የባሕርይ አምላክ ነው" አለ እንጅ "ወልድ ቅብዕ" አላለም። ስለዚህ ስህተቱ የት ላይ እንደሆነ መመርመሩ የሕይዎት መንግስትን ለመውረስ ይጠቅማል ማለት ነው። አምላከ ቅዱሳን ማስተዋሉን ያድላቸው

No comments:

Post a Comment