Friday, June 24, 2016

"እርሱ በተዋሕዶ ሰው የሆነ አምላክ ነው" part 1

"ከመ አሐዱ ውእቱ ባሕቲቱ ውእቱ አምላክ ወሰብእ ኅቡረ" ትርጉሙም "እርሱ በተዋሕዶ ሰው የሆነ አምላክ ነው" ይህንን ቃል የተዋሕዶው ሊቅ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ተናግሮታል። ይህንን እንድጽፍ ያነሳሳኝ ዋናው ነገር ተዋህዶ እና በተዋህዶ ከበረ የሚለው ቃል የተለያየ የሚመስላቸው ብዙ አላዋቂ የሆኑ የቅባት እምነት ተከታዮች ስላሉ ነው። በተዋህዶ ከበረ ሲባል ቃል እና ሥጋ ከተዋሐዱ በኋላ እንደገና ተከፍሎ ቃል ሥጋን አከበረው ማለት የሚመስላቸው ብዙ ምስጢሩ ያልገባቸው፣ቅዱሳን አባቶቻችን የጻፏቸውን ምስጢራት ሲጠቅሱላቸው እውነታውን በመረዳት ፋንታ አፋቸውን ለስድብ የሚከፍቱ፣ እራሳቸውን ብዙ መጻሕፍትን እንዳወቁና ብዙ ምስጢራትን እንደመረመሩ አድርገው የሚያስቡ በተግባር የሚታይ ፍሬያቸው ግን በተቃራኒው የሆነ ብዙ ቅባቶች ሥላሉ እነሱ ይህን እውነታ ይረዱ ዘንድ ቅዱሳን አባቶቻችን በመጻሕፍት ሥለ ተዋሕዶ የተናገሩትን በመጥቀስ መጻፍ እጀምራለሁ። በመጀመሪያ እንዲረዱት የምፈልገው ነገር ተዋሕዶ እና በተዋሕዶ ከበረ የሚሉት ቃላት ትርጉማቸው አንድ እንደሆነ ነው። የተለያየ ትርጉም የላቸውም ሊኖራቸውም አይችልም። አሁን ሊቁ ወደ ተናገረው ቃል ልመለስ " ከመ አሐዱ ውእቱ ባሕቲቱ ውእቱ አምላክ ወሰብእ ኅቡረ" ትርጉሙም " እርሱ በተዋሕዶ ሰው የሆነ አምላክ ነው" ይላል እዚህ ላይ የምንረዳው ግልጽ የሆነ የተዋሕዶን ምስጢር ነው። ተዋሕዶ ምንድን ነው? የሚለውን እንይ ተዋሕዶ የሚለውን በ 3 ከፍለን እንየው እነዚህም ቅድመ ተዋሕዶ፣ ጊዜ ተዋሕዶና ድኅረ ተዋሕዶ ናቸው። በመጀመሪያ ቅድመ ተዋሕዶን ስናይ:— ቅድመ ተዋህዶ ሁለት አካል እና ሁለት ባሕርይ ነው ያሉት ማለትም መለኮታዊ አካል እና ሥጋዊ አካል፣ መለኮታዊ ባሕርይ እና ሥጋዊ ባሕርይ ናቸው። እንግዲህ እዚህ ላይ ልናስተውለው የሚገባ ነገር ቅድመ ተዋሕዶ አንድ ናቸው ማለት እንደማይገባ ነው። ሁለተኛው ደግሞ ጊዜ ተዋሕዶ ነው። በዚህ ጊዜ ደግሞ መለኮታዊ አካል ከሥጋዊ አካል፣ መለኮታዊ ባሕርይ ከሥጋዊ ባሕርይ አንድ የሆኑበት ምሥጢር ነው። ይህም ማለት መለኮታዊ አካል ሥጋዊ አካልን ሳያጠፋ እንዲሁም መለኮታዊ ባሕርይ ሥጋዊ ባሕርይን ሳያጠፋ፣ ሥጋዊ አካልም መለኮታዊ አካልን ሳያጠፋ እንዲሁም ሥጋዊ ባሕርይ መለኮታዊ ባሕርይን ሳያጠፋ በተዐቅቦ በመጠባበቅ፣ ያለ መለወጥ፣ ያለ ኅድረት፣ ያለመመለስ፣ ያለመቀላቀል፣ ያለመለያየት መለከታዊ አካል ከሥጋዊ አካል፣ መለኮታዊ ባሕርይ ከሥጋዊ ባሕርይ ፍጹም አንድ የሆኑበት ምሥጢር ነው። ለዚህም ነው ሊቁ ጎርጎርዮስ " ከመ አሐዱ ውእቱ ባሕቲቱ ውእቱ አምላክ ወሰብእ ኅቡረ" ትርጉሙም " እርሱ በተዋሕዶ ሰው የሆነ አምላክ ነው" ሃይማኖተ አበው ዘጎርጎርዮስ 35 ቁጥር 21ብሎ የተናገረዉ። በዚሁ ምዕራፍ ቁጥር 2 ላይ እንዲህ ይላል " እስመ ክርስቶስ ኢ ፍጡር ወፍጡር ኀብሩ በአሐዱ ህላዌ ወአካል" ትርጉሙም "ክርስቶስ ማለት ፈጣሪና ፍጡር አንድ አካል አንድ ባሕርይ በመሆን አንድ ሆነ ማለት ነው።" ሌላው እዚህ ላይ የምናየው ነገር በተዋሕዶ የመለኮት ገንዘብ ለሥጋ የሥጋ ገንዘብ ለመለኮት መሆኑን ነው። የመለኮት ገንዘብ ምን ምን ናቸው ቢሉ አምላክነት፣ ፈጣሪነት፣ ሁሉን ቻይነት፣ የአብ ልጅ መባል፣ ቃለ አብ መባል፣ ረቂቅነት፣ አለመራብ፣ አለመጠማት፣ ይህን የመሰሉት ሁሉ ናቸው። የሥጋ ገንዘብ የሚባሉት ደግሞ ፍጡርነት፣ መራብ፣ መጠማት፣ ግዙፍነት፣ ውሱንነት፣ ደካማነት፣ ሕማም የሚስማማው፣ ሞት የሚስማማው እና የመሳሰሉት ናቸው። እንግዲህ ዋናው ምሥጢር እዚህ ላይ ነው። በተዋሕዶ ሥጋ የመለኮትን ገንዘብ ገንዘብ አደረገ ማለት ሥጋ የአብ ልጅ መባልን፣ ቃለ አብ መባልን፣ ፈጣሪነትን፣ ሁሉን ቻይነትን፣ የማይመረመር መሆንን ገንዘቡ አደረገ ማለት ነው። መለኮት ደግሞ ከላይ የጠቀስኳቸውን የሥጋ ገንዘቦች ገንዘብ አደረገ እንላለን። ይህንን ስንል ግን የሥጋ ኃጢአት ወደ መለኮት አልተላለፈበትም። ከዚህ ላይ እንደጠቀስኩት በተዋሕዶ ሥጋ አምላክነትን ወልደ አብነትን፣ ቃለ አብነትን ገንዘቡ ካደረገ ከዚህ ሌላ ምንም ምን ተጨማሪ ነገር አያስፈልግም ማለትም ከዚህ በኋላ ቅባቶች እንደሚሉት በመንፈስ ቅዱስ ቅባትነት አብ ሥጋን የተዋሃደ መለኮትን አከበረው አይባልም ይሕ ፈጽሞ ክህደት ነው ምክንያቱም መጀመሪያ በተዋህዶ ሥጋ የቃልን ገንዘብ ገንዘቡ አድርጓልና ነው። እንግዲህ በተዋህዶ ሥጋ የቃልን ገንዘብ ገንዘቡ ካደረገ መለኮተን የተዋሃደ ሥጋ በአብ ልብነት ያስባል፣ በመንፈስ ቅዱስ ሕይዎትነት ከዚህ እስከዚህ ተብሎ ለማይነገር ዘመን ለዘላለሙ ሕያው ሆኖ ይኖራል ማለት ነው። ለዚህም ነው ቅዱስ ጎርጎርዮስ "ወዓዲመ ይትበሀል ፍጡረ በእንተ ዘኮነ ሥጋ ወኀደረ ላዕሌነ ዝንቱ ሶበ ኮነ ሥጋ ከሠተ ስብሐቲሁ በምግባር ከመ እግዚአብሔር አስተርአየ በሥጋ ወውእቱ አምላክ ወልድ ዋሕድ ዘሀሎ ውስተ ሕፅነ አቡሁ" ትርጉሙም " ዳግመኛም ባሕርያችንን ተዋሕዶ ሰው ስለሆነ ሰው ይባላል እርሱ ሰው በሆነ ጊዜ እግዚአብሔር በሥጋ እንደታየ በሥራው ጌትነቱን ገለጠ እርሱ አምላክ ወልድ ዋሕድ በአባቱ ዕሪና ያለ ነው" ብሎ የተናገረው ሥለዚህ በተወህዶ ከበረ ማለት ቅባቶች እንደሚሉት ከተዋሕዶ በኋላ መለኮትና ሥጋ ተለያይተው መለኮት ሥጋን አከበረ ማለት አይደለም ሊሆንም አይችልም። ቅዱሳን አባቶቻችንም እንደዚህ አላሉም የእነሱን አሰረ ፍኖት የምንከተል እኛ የተዋሕዶ ልጆችም አላልንም ወደፊትም አንልም። ይቀጥላል•••

No comments:

Post a Comment