Thursday, June 23, 2016

ማስረጃ ወይስ ሰውን መሸወጃ




ክፍል አንድ
ይህንን ርዕስ ለማየት እንደ መነሻ የማደርገው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዘመነ ስጋዌው ለደቀ መዛሙርቱ ይናገረው የነበረውን ቃል ነው፡፡ ቃሉም እንዲህ ይላል “ይቀልል ኅልፈተ ሰማይ ወምድር እምትደቅ አሃቲ ቃል እም ኦሪት ወእም ነቢያት” ትረጉሙም “ከኦሪት እና ከነቢያት አንዲት ቃል ከምትወድቅ የሰማይ እና የምድር ማለፍ ይቀላል” ነው የሚለው እንግዲህ ከዚህ ቃል ብዙ የምንማረው ነገር አለ፡፡ እግዚአብሔር አምላክ በቅዱሳኑ አድሮ ካናገራቸው እና ካጻፋቸው ቃላት ውስጥ አንድ ሰው በስጋ ፈቃዱ ተነሳስቶ ረዘመ ላሳጥረው፤ አጠረ ላስረዝመው፤ ወይም በምፈልገው መንገድ እንደ እራሴ ሃሳብ እና ምኞት ልተርጉመው ማለት እንደማይገባ ነው፡፡ የጌታችን የኢሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርትም የእግዚአብሔርን ቃል ሰው በፈለገው መንገድ መተርጎም እንደማይገባ አስተምረዋል፡፡ በጻፏቸው የተለያዩ የመጻሕፍት ክፍልም ገልጸውታል፡፡ ከእነሱ በኋላ በየዘመኑ የተነሱ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያንም  ይህንኑ ቃል አጽንተውታል፡፡ በአሁኑ ሰዓትም ቢሆን ቅድስት ቤተክርስቲያን በዓውደ ምህረት ላይ ይህንን ቃል በእውነተኛ መምህራን ልጆቿ አማካኝነት ይህንን ቃል ታስተላልፋለች፡፡ ከዚያም አልፎ በቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ውስጥ ቅዱስ ወንጌል ከተነበበ በኋላ በገባሬ ሰናዩ ቄስ አማካኝነት ይህንን ቃል ታውጃለች፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሔርን ቃላት በምናነብበትም ሆነ በምንማርበት ጊዜ አንዲት ቃል እንኳ ተሳስተን እንዳንተረጉም መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ግን እራሳቸውን እንደ አዋቂ የሚቆጥሩ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል ለእራሳቸው በሚመች መንገድ መተርጎም ጀምረዋል ስለዚህ ጌታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ “ከፈሪሳውያን እና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠበቁ” ብሎ ለሐዋርያት እንደነገራቸው እኛም እራሳችንን ከእንደነዚህ አይነት ሰዎች ልንጠብቅ ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ያልኩበት ምክንያት አንድ አዲሱ የሚባል እና መሰሎቹ(ቅብዓቶች) ለተጠየቁት መልስ ሲመልሱ እና ማስረጃ ብለው ያቀረቧቸው የቃላት ትርጉም ቅዱሳን አባቶቻችን በአንድምታ መጻሕፍት ከተረጎሙት ውጭ ሆኖ ስላገኘሁት ነው፡፡ለማነጻጸር ያመቸን ዘንድ ልጁ የተረጎመውን እና በመጽሐፉ ላይ ያለውን እንድምታ ትርጉም  እንደሚከተለው አንድ በአንድ እናያለን፡፡ ይቀጥላል

2 comments:

  1. ቦታህን፣ ስምህን እየቀየርክ ሰላሳ ጊዜ በየ ድረ ገጹ ብትለጥፍ "እውነት ያው እውነት፤ ሀሰትም ያው ሀሰት" እስከሆነ ድረስ ምንም አዲስ ነገር የለም:: ምንም እንኳን አንተ መጽሐፍትን በቅርቡ አግኝተው የማያናቡ ምዕመናንን ልትሸውድ ትችል ይሆናል ነገር ግን መጽሐፈ ምስጢር ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም መጽሐፍት እያነበበ፣ ንባብ ከነትርጓሜው እያስማማ የሚያነብ ሰው ግን በአንተ ከንቱ ፍልስፍና ሊሸወድ አይችልም፤ ምክንያቱም ቅ/ጳውሎስ"ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ፥ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ፥ የተረገመ ይሁን" ገላ 1፥8 ብሎ ተናግሯልና:: እስኪ አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ "እግዚአብሔር አለኝ። አንተ ልጄ ነህ፥ እኔ ዛሬ ወለድሁህ"መዝ 2፥7 ይላልና ቅዱስ ዳዊት "ዛሬ" ብሎ የተናገረው ለቀዳማዊ ልደቱ ነው ወይንስ ለድኃራዊ ልደቱ ነው? ለቀዳማዊ ልደቱ እንዳይባል ቅዱሳን አበው በሃይማኖተ አበው "ቀዳማዊ ልደቱ በድኃራዊ ልደቱ ታወቀ" እንዳሉት ቅድመ ልደቱ ዓለም ሳይፈጠር ዘመን ሳይቆጠር የተወለደ ስለሆነ "ዛሬ" ተብሎ ለቅድመ ልደቱ አይነገርለትም:: ስለዚህ "ዛሬ ወለድኩህ" ያለው የትኛውን ልደቱን ያመለክታል?

    ReplyDelete
    Replies
    1. አንተ ማንበብ ስለማትች እንጅ ሁሉም ከላይ ተጽፎልሃል

      Delete