Saturday, May 6, 2017

“እርሱ በተዋሕዶ ሰው የሆነ አምላክ ነው”

“እርሱ በተዋሕዶ ሰው የሆነ አምላክ ነው”፡፡ በሚል ርእስ በክፍል አንድ እና ሁለት ተዋሕዶን ሊቁ የተዋሕዶ አርበኛ ቅዱስ ጎርጎርዮስ እንዴት እንደገለጸው አይተናል፡፡ በዚህ ክፍል ደግሞ ሊቁ ቅዱስ ቄርሎስ ተዋሕዶን ለማስረዳት የመሰለውን ምሳሌ እናያለን፡፡ ከዚያ በፊት ግን ይህንን ጽሁፍ የምታነቡ ሰዎች እንድትረዱኝ የምፈልገው ነገር እኔ አባቶች በመጽሐፋቸው ላይ ያሰፈሩትን ነገር ሳልጨምር ሳልቀንስ እንደምጽፈው ልገልጽላችሁ እፈልጋለሁ፡፡ የቅባት ተከታዮች ግን እነሱ የማያውቁት ነገር ከሆነ ወይም እነሱ የሚሉትን የኑፋቄ ትምህርት የሚደግፍ መስሎ ካልታያቸው ምዕራፍ እና ቁጥር ጠቅሼ የጻፍኩትን ጽሁፍ የእራስህ ፍልስፍና ነው በማለት እነሱ እንደማይቀበሉት በክፍል አንድ እና ሁለት በሰጡት አስተያየት ላይ ለማየት ሞክሬያለሁ፡፡ ይህ ግን ፈጽሞ ከእውነት የራቀ ነው፡፡ ስለዚህ የእነሱን ማንነት ለመረዳት የሚጠቀሰውን ጥቅስ መጽሐፉ ላይ በመሔድ ማንበብ እና እውነት ወይም ሐሰት መሆኑን መረዳት ትችላላችሁ፡፡ወደ ምሳሌው ከመሔዴ በፊት የቅባት እምነት ተከታዮች ምስጢረ ስላሴ ላይ ያልገባቸው ነገር እንዳለ ትንሳኤ የሚባል ተከታያቸው ከጻፈው ጽሁፍ መረዳት ችያለሁ፡፡ ሌሎች የጻፋቸውን ነገሮች በሚቀጥሉት ከፍሎች እናያለን፡፡ መልካም ንባብ ካነበባችሁ በኋላ ሼር ማደረግን እንዳትረሱ ምክንያቱም ለሌሎች የድህነት ምክንያት ይሆናል እና ነው፡፡
ስላሴ ሶስት ከሚሆኑባቸው ነገሮች አንዱ የከዊን ሶስትነት ነው፡፡ ይህም ከዊነ ልብ፣ ከዊነ ቃል እና ከዊነ እስትንፋስ ናቸው፡፡ ምንም እንኳ ስላሴ በከዊን ሶሰት ቢሆኑም በህልውና በመገናዘብ ደግሞ እንድ ይሆናሉ፡፡ ይህም እንዴት ነው ብትሉ እንደሚከተለው ነው፡፡ ይህም ማለት በአብ ልብነት ወልድም መንፍስ ቅዱስም ያስቡበታል፡፡ በወልድ ቃልነት አብም መንፈስ ቅዱስም ይናገሩበታል፡፡ በመንፈስ ቅዱስ እስትንፋስነት(ሕይወትነት) አብም ወልድም ለዘለዓለም ሕያዋን ሆነው ይኖሩበታል፡፡ ይህ በስላሴ በህልውና የመገናዘብ ሁኔታ ቀድሞም አልተለያየም፡፡ አሁንም አልተለያየም፡፡ ወደፊትም ቢሆን አይለያይም፡፡ ይህና ያመጣሁበት ዋናው ምክንያት ሰው ምስጢረ ተዋሕዶን ለመረዳት መጀመሪያ ይህንን ረቂቅ ምስጢር መረዳት ስለሚገባ ነው፡፡ ትንሽ ስለረዘመ ነው ምሳሌው በክፍል አራት ይቀጥላል፡፡

ማስረጃ ወይስ ሰውን መሸወጃ


ክፍል ሁለት
1. መዝ 2÷7 “ እግዚአብሔር ይቤለኒ ወልድየ አንተ ወአነ ዮም ወለድኩከ” የሚለውን አዲሱ ሲተረጉም ፡- “እግዚአብሔር ይቤለኒ ወልድየ አንተ” ማለቱ እምቅድመ ዓለም ከአብ የተወለደውን ልደት ሲናገር ነው፡፡ “ወአነ ዮም ወለድኩከ” ማለቱ መለኮት ሰው ሲሆን በማኅጸነ እግዝእትነ ማርያም በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ የተወለደውን ልደት ሲናገር ነው፡፡ በማለት እንደ እራሱ ፈቃድ ይተረጉመዋል፡፡ ከዚህ በመቀጠል ደግሞ ከዳዊት አንድምታ ትርጓሜ መጽሐፍ ላይ ያለውን ትርጉም እንይ
መዝ 2÷7 “ እግዚአብሔር ይቤለኒ ወልድየ አንተ” ትርጉም አሁን አንተን አይሻም (ቃል ይቤ በል) ቅድመ ዓለም አካል ዘእም አካል ፣ ባህርይ ዘእም ባህርይ የወለድኩህ ልጄ ነህ አለኝ፡፡
“ወአነ ዮም ወለድኩከ” የሚለው ደግሞ ሲተረጎም ፡- አሁንም አነ ን አይሻም ዛሬም በተዋኅዶ የወለድኩህ ልጄ ነህ አለኝ፡፡ “ተውህቦ ለእግዚአብሔር ቃል ስም በስጋ ዘበ ህላዌሁ ይሰመይ” እንዲል ስለ ስጋ እንግድነት ሲገልጽ
አንድም፡-“ ሥጋ ይቤ” ይልና ፡- አንተ ሥጋ ቅድመ ዓለም አካል ዘእም አካል ባሕርይ ዘእም ባሕርይ የወለድኩህ ልጄ ነህ አለኝ፡፡ አንተ ልጄ ነህ ዛሬም በተዋህዶ ወለድኩህ ማለት በቃል ርስት፡፡
አንድም ፡- አሁንም አንተን እና አነን አይሻም(ስግው ቃል ይቤ)፡- ቅድመ ዓለም አካል ዘእም አካል ባሕርይ ዘእም ባሕርይ የወለድኩህ ልጄ ነህ አለኝ ፡፡ ዛሬም አውጻእኩከ አንሳእኩከ ሲል ነው፡፡ በትንሳኤ የወለድኩህ ልጄ ነህ አለኝ፡፡ አሁን ሁለተኛ የሚወልደው ሆኖ አይደለም በምሳሌ ተናገረው እንጅ ሰው ዘምቶ ያረጃል፤ በልቶ ያፈጃል፤ ህዝብን ሰብስቦ ልጁን አስጠርቶ ልጄ ‹‹ዘምቶ ያረጀ በልቶ ያፈጀ ›› ይሉሃል እኔ ነኝ፡፡ ‹‹በርስቴ ውጣበት ውረድበት›› ብሎ ይሰጠዋል፡፡ እሱም ወጣሁ ልጅ ነኝ ፈላሁ ጠጅ ነኝ ብሎ እግሩን ለጠጠር ደረቱን ለጦር ሰጥቶ ይዘምታል፡፡ በርስቱ ርስት በጉልቱ ጉልት ጨምሮበት ይመጣል፡፡ አባቴ በሰጠኸኝ ርስት ጉልት ጨምሬበት መጣሁ ይለዋል፡፡ እርሱም ቀድሞም ልጄ ዛሬም ልጄ ይልቅስ የዛሬው ይብለጥ ይለዋል፡፡ ጌታም ከአቤል ጀምሮ እስከ ዕለተ ዓርብ ያሉትን ነፍሳት “እለ ውስተ ሲኦል ፃዑ ወእለ ውስተ ጽልመት ተከስቱ ወርእዩ ብርሐነ ዐቢየ” በገነት አድርጎ ባረገ ጊዜ ልጄ ነህ አለው እንጅ፡፡
ወገኖቸ እንግዲህ እናንተ ፍረዱት ከመዝሙረ ዳዊቱ አንድምታ ላይ ያለው እውነታ ይህ ነው፡፡ መጽሐፉን ገዝታችሁ ማንበብ ትችላላችሁ፡፡ ከአንድምታው ላይ እንዳየነው “ወአነ ዮም ወለድኩከ” የሚለው “መለኮት ሰው ሲሆን በማኅጸነ እግዝእትነ ማርያም በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ የተወለደውን ልደት ሲናገር ነው” የሚል ትርጉም የለውም፡፡ ስለዚህ አዲሱ እና መሰሎቹ የቅብዓት ተከታዮች ለራሳቸው እምነት እንዲመች አድርገው የጨመሯት ትርጉም ናት ማለት ነው፡፡ ይኸውም “ወልደ አብ” በተባለው መጽሐፋቸው ላይ የጠቀሷትን “በማኅጸነ እግዝእትነ ማርያም በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ከአብ ተወለደ” የምትለዋን አዲስ ፍልስፍናቸውን እውነታ ለማስመሰል የተጠቀሙት የማጭበርበሪያ ዘዴ ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሰዎች ማስረጃ እያሉ በተለያየ ጊዜ የሚጠቅሱትን የጥቅስ ጋጋታ ሁሉ ቅዱሳን አባቶቻችን በየዘመኑ ተነስተው ከጻፉት አንድምታ ጋር በማገናዘብ ስህተታቸው የት ላይ እንዳለ ልናሳውቃቸው ያስፈልጋል፡፡ እኛም እውነት መስሎን በሚጠቅሱት ጥቅስ ምክንያት ተደናግረን ከእውነተኛዋ መንገድ እንዳንወጣ መጠንቀቅ እና መትጋት ያስፈልጋል፡፡ ይቀጥላል