Friday, September 19, 2014

የኤሊ እና የጥንቸል ውድድር (ክፍል 1)


በአንድ አካባቢ ባማረና በተዋበ ግቢ የምትኖር አንድ ኤሊ ነበረች፡፡ በዚያው አካባቢ በምድረ በዳ የምትኖር አንዲት ጥንቸል ነበረች፡፡ ይህች ጥንቸል ማለፊያ መንገዷ በኤሊዋ መኖሪያ አጠገብ ስለነበር ጠዋት ማታ ስትመላለስ ኤሊዋን እያየች እጅግ ትቀናና እንዴት እንደምታስወጣት እና እርሷ ከዚያ ቦታ እንደምትገባ ታስብ ነበር፡፡ በዚህ ሃሳብ እየኖረች እያለ አንድ ቀን ልዩ ሃሳብ መጣላት፡፡ ይሄውም ውድድር መወዳደር ነው፡፡ ጥንቸሏ ይህን ሃሳብ ያሰበችው ኤሊዋን በሩጫ ውድድር እንደምትቀድማት ስላሰበች ነው፡፡ ይህን ሃሳብ ይዛ ወደ ኤሊዋ ሄደችና ነገረቻት እንዲሁም በውድድሩ የተሸነፈ ባማረና በተዋበው ግቢ ሊኖር እንደሚገባ አስረዳቻት፡፡ ኤሊዋም በሃሳቡ ተስማማችና የውድድሩን ቀን ቆርጠው ተለያዩ፡፡ የውድድሩ ቀን በደረሰ ጊዜ ሁለቱም በቦታው ተገኝተው ውድድሩ ተጀመረ፡፡ እንደተጀመረም ጥንቸሏ እንደ ሚስያል ተወንጭፋ ኤሊዋን ቀድማት ሄደችና ዞራ ስታይ ኤሊዋ ያለችበት ቦታ አይታይም፡፡ በዚህም ጊዜ ኤሊዋ በኔ መድረስ ስለማትችል ትንሽ ልተኛ ብላ እንቅልፏን ለጥ አለች፡፡ ኤሊዋም ተስፋ ሳትቆርጥ በጥንቸሏ ለመድረስ ትሮጥ ነበር፡፡ በዚህም ጊዜ ጥንቸሏ ተኝታ ስለነበር ኤሊዋ ቀድማ በመግባት ውድድሩነ በድል አጠናቀቀች፡፡ ጥንቸሏ ከእንቅልፏ ስትነቃ በኤሊ እንደተሸነፈች ተረዳች፡፡ በአሁኑ ወቅትም ብዙ ሰዎች እንደ ጥንቸል በሌሎች መልካም ኑሮ የሚቀኑ አሉ፡፡ የጥንቸል ፍላጎት ኤሊዋ ከምትኖርበት የተደላደለ ህይዎት ማሰወጣት ነበር፡፡ ዛሬ ዛሬ እንደ ጥንቸል አይነት ብዙ ሰዎች ሌሎች በልተው ስላደሩ፣ ልብስ ስለለበሱ፣ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ስላገኙ እና ጥሩ በሆነ የቤተሰብ አኗኗር ስለኖሩ ብቻ በቅናት መንፈስ ተነሳስተው ሰዎችን ወደ ጥልቅ የዉድቀት ጉድጓድ ለመጣልና ህይዎታቸውን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት የሚሮጡ ሆነዋል፡፡ ሆኖም ግን በሌሎች ተንኮልና የቅናት መንፈስ ሳይጨነቁ እንደ ኤሊ ተስፋ ሳይቆርጡ ስራቸውን በትግስት የሚሰሩ ሰዎች በሰዎች ዘንድ የተጠሉ ቢሆንም እና እስከ ሞት ድረስ የሚያደርስ መከራ ቢገጥማቸውም ሁሉን በጸጋና በትግስት ከተቀበሉት ፍጻሜያቸው ያምራል፡፡ ኤሊዋ ጥንቸሏን በመቅደም እነዳሳፈረቻት ሁሉ እንደ እሷ አይነት ሰዎችም ተስፋ ሳይቆርጡ በህይዎታቸው ተግተው የሚኖሩ ከሆነ ፈተናውን ሁሉ አልፈው ሲቀኑባቸው የነበሩ ሰዎችን አፍ ማስያዝና የድል አክሊልን መቀዳጀት ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ተስፋ ሳንቆርጥ ስራችንን በመስራት በአገራችን ላይ ያሉ ሳይሰሩ ነገር በማመላለስ ብቻ በሰው ጫንቃ ላይ ተቀምጠው የችግረኞችን እድል ወደ ራሳቸው በማጠፍ የሰው ደም እየጠጡ የሚኖሩ ሰዎችን  እውነታውን በመግለጽ ልናሳፍራቸው ያስፈልጋል፡፡ መጀመሪያ ግን ራሳችንን ለመፈተሽ ያህል  ስንቶች ነን እንደ ጥንቸሏ ሆነን የምንኖር? እንደ ኤሊዋስ?
ይቀጥላል....

Monday, September 15, 2014

"መጥፎውን ሽሹ መልካሙን እሹ እና ትውልዱን እንታደገው ትውልዱ እኛ ነን": ተሐድሶ መናፍቃን ክፍል አንድ

"መጥፎውን ሽሹ መልካሙን እሹ እና ትውልዱን እንታደገው ትውልዱ እኛ ነን": ተሐድሶ መናፍቃን ክፍል አንድ: ተሐድሶ መናፍቃን ምንፍቅና ዛሬ ሳይሆን ገና በፍጥረት መጀመሪያው ዕለት በሳጥናኤል አንድ ብሎ የጀመረ መርዝ ነው፡፡ ከዚያም በኋላ ዲያብሎስ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ  ሰዎችን በምንፍቅና ሲያሰለጥናቸው ቆይቷል፡፡ ...

Tuesday, September 9, 2014

ኦ ማርያም በእንተዝ ናፈቅረኪ ወናዓብየኪ


“ኦ ማርያም በእንተዝ ናፈቅረኪ ወናዓብየኪ”

 “ማርያምሆይ ስለዚህ ነገር እንወድሻለን እናገንሻለን”
ይህንን ቃል የተናገረው አባ ሕርያቆስ ሲሆን ተጽፎ የምናገኘው በቅዳሴ ማርያም ውስጥ ነው፡፡ አባቶቻችን የእግዚአብሔር መንፈስ ስላደረባቸውና የእመቤታችንን ክብር ስለተረዱ እመቤታችንን ያመሰግኗት ነበር፡፡ ሊቁ ስለዚህ ነገር እናከብርሻለን እናገንሻለን ካለ በኋላ “እስመ ወለድኪ ለነ መብልዓ ጽድቅ ዘበአማን ወስቴ ሕይወት ዘበአማን” “እውነተኛ የሕይወት መብልንና የሕይወት መጠጥን ወልደሽልናልና” አለ፡፡ ከዚህ የምንረዳው ነገር እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዓለም ሳይፈጠር በአምላክ ኅሊና ታስባ ትኖር የነበረች በኋላም ለአዳም የሰጠው የተስፋ ቃል ሲደርስ እውነተኛ የሕይወት መብልና የሕይወት መጠጥ የሆነውን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመውለድ በቅታ የተገኘች እውነተኛ እናታችን ናት፡፡
በእውኑ ስለ ድንግል ማርያም ያልተናገረ ማን ነው? እሷንስ ያላወደሰ ማን ነው? በእውነተኛ ህሊና ሆነን ካሰብነው ሌሎች መናፍቃን እንደሚሉት ድንግል ማርያምን ለማመስገን እና ለማወደስ እንዲሁም ለድንግል ማርያም የጸጋ (የአክብሮት) ስግደት ለመስገድ የግድ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ አያስፈልግም:: ሰው ሁኖ መፈጠር ብቻ በቂ ነው፡፡ ምክንያቱም ቅዱስ ዮሐንስ በእናቱ ማኅጸን እያለ ቅድስት፣ ክብርት፣ ልዩ ለምትሆን ለድንግል ማርያም የሰገደው  መጽሐፍ ቅዱስን አንብቦ ወይም ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ፈልጎ ስላገኘ እንዳልሆነ ሁላችን የምናውቀው እውነታ ነው፡፡ እርሱ የሰገደላት እውነተኛ ሰው ሁኖ በመፈጠሩ ብቻ ለድንግል ማርያም የተሰጣትን አምላክን የመውለድ ልዩ ስጦታ(ጸጋ) ስላወቀ ነው፡፡ አባቶቻችን  ስለ ድኅነት ሲያስተምሩ፣ ሲጽፉ እና በምሳሌም ሲናገሩ ብቻ ሳይሆን በሕይወታቸው ውስጥም ያለ ድንግል ማርያም የኖሩበት ጊዜ የለም ነበር ወደፊትም አይኖርም፡፡ እዚህ ላይ ነቢየ እግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ የተናገረውን ነገር እናንሳ (መዝሙር 44፡14 ጀምሮ ያለውን) ‹‹ወለገጽኪ ይትመሐለሉ ኩሎሙ አሕዛብ ብዑላነ ምድር›› ‹‹ገጸ ምሕረትሽን፣ ገጸ ረድኤትሽን ለማግኘት፤ አንድም በቁሙ(በቀጥታ በጥሬ ትርጉሙ)  በዚህ ዓለም የከበሩ የገነኑ ህዝቦች ሁሉ ፊትሽን ለማየት ይለምናሉ፡፡ እዚህ ላይ የምንረዳው ነገር የእመቤታችን የድንግል ማርያም ክብሯ  አፍአዊ፣ ምድራዊና ስጋዊ ሳይሆን ውሳጣዊ፣ ሰማያዊ እና መንፈሳዊ ነው፡፡ይህም ማለት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ንጽሐ ስጋ፣ ንጽሐ ነፍስ እና ንጽሐ ልቡናን አስተባብራ የያዘች ልዩ ፍጥረት ስለሆነች ቅዱሳን አባቶቻችን ገጸ ረድኤቷን ለማግኘት ሁሉ ጊዜ በትጋት ይለምናሉ፡፡  አንድ አባ ይስሐቅ የሚባል ቅዱስ ‹‹አርእየኒ እመከ›› ‹‹እናትህን አሳየኝ›› እያለ ሰባት ዓመት ሲጸልይ ኖሯል፡፡ ከዚያም በኋላ እመቤታችን ተገልጻ እረፍትህ ደርሷል፡፡ ክፍልህ ከእኔ ነው ብላው አርጋለች፡፡(ተአምረ ማርያም) ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ቅዱሳን አባቶቻችን እመቤታችንን ያመሰግኑ የነበሩት መጽሐፍ ቅዱስ አላነብ ብለው ነው?  አይደለም፡፡ እነሱማ ከማንበብም አልፈው በሕይዎትም ተርጉመው እየኖሩበት ነው፡፡ መቸም ሁላችንም እንደምናውቀው መጽሐፍ ቅዱስን ከማንበብ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስን አንብቦ በሕይዎት መኖር ይበልጣል፡፡ ምክንያቱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዘመነ ስጋዌው ሲያስተምር “ይህንን ቃል አንብቦ፣ ተምሮ እና አስተምሮ ነገር ግን ወደ ተግባር(ወደ ሕይዎቱ የማያስገባው)፣ ወደ ስራ የማይለውጠው ሰው ፊቱን በመስታዎት የሚያይ ሰውን ይመስላል” ብሎ ተናግሯል፡፡ ስለዚህ አባቶቻችን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን የማመስገናቸው ታላቁ ምስጢር መጽሐፍ ቅዱስ አላነብ ብለው ሳይሆን ከአምላክ የተሰጣትን ልዩ የሆነ ክብሯን አምላክ በገለጸላቸው መጠን መረዳት መቻላቸው ነው፡፡ ስለዚህ እኛም በዚህ ዘመን ያለን ትውልዶች ሁሉ በቅድስናም ሆነ በእውቀት ከአባቶቻችን አንበልጥምና እውነተኛ የሕይወት መብልና መጠጥ የሆነውን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ለማግኘት ማደሪያ ትሆነው ዘንድ የመረጣትን ድንግል ማርያምን ማክበርና ማመስገን ይገባል፡፡ አምላካችን ድንግል ማርያምን የምናመሰግንበት መልካሙን አንደበት ክብሯን የምናይበት ውሳጣዊ ዓይነ ኅሊና ያድለን፡፡ አሜን፡፡