Friday, June 24, 2016

"እርሱ በተዋሕዶ ሰው የሆነ አምላክ ነው" ክፍል 2

በክፍል አንድ ላይ እንዳየነው በተዋሕዶ ከበረ ማለት በተዋሕዶ የመለኮት ገንዘብ ለሥጋ የሥጋ ገንዘብ ደግሞ ለመለኮት ሆነ ማለት ነው። በተዋሕዶ አምላክ ፍጹም ሰው ሆነ ሰውም ፍጹም አማላክ ሆነ ማለት ነው። ከዚህ ውጭ ሌላ ትርጉም የለውም። በራሱ ፍላጎት እና ትርጉም ከዚህ ውጭ ትርጉም አለው የሚል ሰው ካለ እርሱ አባቶቻችን ካስተማሯት እምነት ውጭ ነው ማለት ነው። ይህንን ሲገልጽ ሊቁ ጎርጎርዮስ እንዲህ ብሏል "ወለአስተርእዮቱሂ ለነ በሥጋ ኢይትከሀለነ ናእምሮ ዘከመ ድልወቱ ወበእንተ ዝንቱ ያጌብረነ ንትመሀር እም እሉ መምህራን ዘይቤ ቃል በእንቲአሆሙ ይደሉ ይትወከፉ እምኔሆሙ ኩሎሙ እለ ይሰምዑ ቃለ በእንተ ምሥጢር ዐቢይ ዘለኂሩት" ትርጉሙም "ለእኛም በሥጋ መገለጡን እንደሚገባው መርምረን ልናውቀው አይቻለንም። ጸጋን ለመስጠት ያደረገውን ተዋሕዶ የሚያምኑት ሰዎች ከእነርሱ ትምህርትን ይቀበሉ ዘንድ ይገባል ብሎ ቃል ስለ እነርሱ ከተናገረላቸው ከመምህራን እንማር ዘንድ ያሻናል" ብሏል። ቀጥሎም "ዝንቱ ቃል ዘአስተርአየ በሥጋ በእንቲአነ እንዘ ውእቱ በአርአያ እግዚአብሔር" ትርጉሙም " ይህ እግዚአብሔርን በመልክ የሚመስለው በባሕርይ የሚተካከለው ሲሆን ቃል ስለ እኛ በሥጋ የታየው መታየት ነው" " ወኮነ ምስለ ሰብእ በአርአያ ገብር በሥጋ ዝንቱ ዘአልቦቱ ጥንት ተወክፈ ሎቱ ለባሕቲቱ ህላዌ ሥጋ ዘቦቱ ጥንት ዘነሥአ እም እግዝእትነ ቅድስት ድንግል ማርያም ንጽሕት ዘእንበለ ርስሐት" ትርጉሙም "በተገዥ በአዳም ባሕርይም በሥጋ የሰውነትን ሥራ ሠራ ጥንት የሌለው እርሱ ያለ መለወጥ ንጽሕት ከምትሆን ከቅድስት ድንግል ማርያም የነሣውን ጥንት መገኛ ያለውን የሥጋን ባሕርይ በተለየ አካሉ ተዋሐደ" ሃይማኖተ አበው ዘጎርጎርዮስ ምዕራፍ 35 ቁጥር 10—12 ከጊዜ አንጻር ሁሉን መጥቀስ ስለማይቻል መጽሐፉን ግዙና አንብቡት። አባቶቻችን ያስተማሯት ተወሕዶ እምነት ይህች ናት። አሁን እኛ ቅባቶችን እያልናቸው ያለ "ሥጋ በተዋሕዶ የመለኮትን ገንዘብ ገንዙቡ አድርጎ የባሕርይ አምላክ ከሆነ፣ የአብ ልጅ ከሆነ፣ የአብ ቃል ከሆነ፣ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ ሕይወቱ ከሆነ" ሥጋ እነዚህን የመለኮት ባሕርያት በተዋሕዶ እንዳላገኘ አድርገው "አብ በመንፈስ ቅዱስ ቅብነት ሥጋ የተዋሐደ ቃልን አከበረው ማለት ለምን አስፈለገ? ዋናው ጥያቄ ይህ ነው። እንግዲህ የሚያስተውሉ ከሆነ ይህንን ይመርምሩ እንቢ አሻፈረኝ ብለው ሰውን መሳደብ እና ማጠጣል ከሆነ ግን "ዘቦ እዝን ሰሚዐ ለይስማእ" ብለን ዝም እንላቸዋለን። እኛ ግን እውነታውን ከመናገር እና ከመጻፍ ወደኋላ አንልም። ሦስተኛው ከተዋሕዶ በኋላ ያለው ነው። ከላይም ለመግለጽ እንደሞከርኩት ከተዋሕዶ በኋላ ሁሉትነት ጠፍቶ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ሆኗል የሚለው ነው። በማቴዎስ ወንጌል "ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ዘአፈቅር ዘቦቱ ሠመርኩ" ትርጉሙም "የምወደው በእርሱ ህልው ሆኘ ልመለክ የወደድሁት ልጄ ይህ ነው" አለ ማቴ 3:17
ቀጥሎም እንዲህ አለ "ኢኮነ ዝንቱ አሐዱ ክልኤተ፣ ካልእ ወልድየ ወካልእ ወልደ ማርያም፣ አኮ ካልእ ዘተወልደ በውስተ በአት ወአኮ ካልእ ዘሰገዱ ሎቱ ሰብአ ሰገል አኮ ካልእ ዘተጠምቀ ወአኮ ካልእ ዘኢተጠምቀ አላ ውእቱ ወልድየ ፍቁር ዘቦቱ ሠመርኩ" ትርጉሙም "ይህ አንዱ ሁለት አይደለም ልጄ ያለው ሌላ ከማርያም የተወለደው ሌላ አይደለም። በበረት የተወለደው ሌላ ሰብአ ሰገል የሰገዱለት ሌላ አይደለም። የተጠመቀው ሌላ አይደለም ጥምቀት የማያሻውም ሌላ አይደለም። በእርሱ ህልው ሆኘ ልመለክበት የወደድኩት ልጄ ነው እንጅ" ብሎ ሊቁ በማቴዎስ ወንጌል የተነገረውን ቃል አመስጥሮታል። ( ሃይማኖተ አበው ዘጎርጎርዮስ ምዕራፍ 35 ከቁጥር 14 ጀምሮ ያለውን አንብቡት ) እንግዲህ ተዋሕዶ ማለት ይህች ናት። ከዚህ ውጭ የሆነ ትምሕርት የለም በዚች እምነት ጸንተን እንድንኖር የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት የቅዱሳን መላእክ ተራዳኢነት እና የቅዱሳን አባቶቻችን በረከት እና ጸሎት ይርዳን አሜን።

No comments:

Post a Comment